የ2012 ፕሪምየር ሊግ ትናት ሲጀምር የውድድር ዘመኑ የመጀመርያ ጎል በ16ኛው ደቂቃ በድሬዳዋ ከተማ አማካይ ኤልያስ ማሞ ተመዝግቧል። ሶከር ኢትዮጵያም ኤልያስ ማሞ የሊጉን የመጀመርያ ጎል አስቆጣሪ በመሆኑ የተሰማውን እና በወቅታዊ አቋሙ ዙርያ ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አቀረብነው።
በሊጉ የመጀመርያ ጎልህን መቼ አስቆጠርክ፤ ከዚህ ጥያቄ ልጀምር ?
ለጊዜው ወቅቱን ባላስታውስም ቅዱስ ጊዮርጊስ እያለው አስታውሳለው መከላከያ ላይ ነው። የመጀመርያ በእግርኳስ ህይወቴ የመጀመርያ የሊጉን ጎል ያስቆጠርኩት።
የ2012 የውድደር ዘመን የመክፈቻ ጨዋታ የመጀመርያ ጎል አስቆጥረሀል…
አዎ የመጀመርያ ጎል አስቆጣሪ መሆኔን የሰማሁት ከጨዋታው በኋላ ነበር። እኔ እንደምሆን አልጠበኩም ነበር። ያው በውጤቱ ባዝንም ይሄን በመስማቴ በጣም ተደስቻለው።
ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያለህ ቆይታ እንዴት ነው?
መልካም የሚባል ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው። ዘንድሮም ከዝግጅት ጀምሮ ጥሩ ነገር ሰርተን ወደ ውድድር ገብተናል። ምንም እንኳ ውድድሩን በሽንፈት ብንጀምርም እንቅስቃሴያችን መልካም የሚባል ነበር። ለቀጣይ ጨዋታዎች ያለውን ነገር አሻሽለን ከቡድን ጓደኞቼ ጋር በመሆን የተሻለ ነገር እናመጣለን ብዬ አስባለው።
ወደ ግል አቋምህ ስመጣ ከቅርብ ወራት ጀምሮ የተረጋጋ ኤልያስን በወጥ አቋም መመልከት አልቻልንም። ታየት ጠፋ እያልክ ነው፤ ምንድነው ምክንያቱ?
2011 ለእኔ መልካም የሚባል ዓመት አልነበረም። በአቋሜም በጤናም በብዙ ነገር መጥፎ ጊዜ አሳልፌያለው። ዘንድሮ ግን ወደ ቀድሞ አቋሜ በሚገባ ለመመለስ ተዘጋጅቻለው። ከፈጣሪ ጋር ከሙሉ ጤንነት ጋር እገኛለው። የተሻለ ነገር አሳያለው ብዬ አስባለው።
ጎል ማስቆጠርህ የተሻለ ነገር እንድትሰራ ያነሳሳህ ይሆን ?
አዎ ጎል ማስቆጠሬ አስተዋፆኦ አለው። ጎል በምታስቆጥርበት ወቅት በራስ መተማመንህ ይጨምራል። በቀጣይም ጨዋታዎች እንዲህ ያለ ነገር ነው የማስበው፤ አሪፍ ጊዜም አሳልፋለው።
© ሶከር ኢትዮጵያ