በስታዲየማቸው እድሳት ምክንያት በአዲስአበባ ስታዲየም የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሰበታ ከተማዎች በወልዋሎ የ3ለ1 ሽንፈት አስተናግደዋል።
በዛሬው ጨዋታ አዲስአበባ ስታዲየም ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ለወትሮው ተመልካች ይገባባቸው የነበሩ በተለያዩ የስታዲየሙ ክፍል የሚገኙ በሮች ተዘግተው ተስተውሏል።
ወልዋሎዎች በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ከተጠቀሙበት የቡድን ተጫዋቾች ውስጥ በርካታ ተጫዋቾች የሚና ለውጥ በማድረግ ጨዋታውን ጀምረዋል፤ በዚህም ካርሎስ ዳምጠው በፊት አጥቂነት፣ አቼምፓንግ አሞስ በመሀል ተከላካይነት እንዲሁም ፍቃዱ ደነቀ፣ ሳሙኤል ዮሐንስና ገናናው ረጋሳ በአማካይ ስፍራ ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል።
ከኳስ ውጭ ወልዋሎዎች በተደራጀ መልኩ በመከላከል እንዲሁም ኳስ በእግራቸው ስትገባ በቀጥተኛ አጨዋወት በፍጥነት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል በዚህም በጨዋታው ከተጋጣሚያቸው በተሻለ አንፃራ የግብ ሙከራዎች የበላይነት ነበራቸው፤ በ9ኛውና በ29ኛው ደቂቃ ኢታሙና ኪይሙኒና ጁኒያስ ናንጂቡ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ተጠቃሽ ናቸው።
ሰበታ ከተማዎች በዛሬው ጨዋታ እምብዛም የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ያልነበራቸው ሲሆን የተደራጀውን የወልዋሎ የመከላከል አደረጃጀት ለማለፍ በእጅጉ ተቸግረው ተስተውሏል።
በ39ኛው ደቂቃ ኢታሙና ኬይሙኒ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ካርሎስ ዳምጠው አስቆጥሮ ቡድኑ 1ለ0 እየመራ ወደ እረፍት እንዲያመራ አስችሏል። ይህች ጎል በውድድር ዘመኑ በፍፁም ቅጣት ምት የተገኘች የመጀመርያ ጎል ሆናም ተመዝግባለች።
ከእረፍት መልስ የግቧ ባለቤት ካርሎስ ዳምጠው ባጋጠመው ጉዳት በወጣቱ ሰመረ ሀፍታይ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ገና ከጅምሩ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ሰበታዎች በ48ኛው ደቂቃ ዳዊት ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ታደለ መንገሻ በግንባሩ ቢገጭም አብዱልአዚዝ ኬይታ በአስደናቂ ብቃት ሊያድንበት ችሏል። ነገርግን በ52ኛው ደቂቃ አዲስ ተስፋዬ የኢታሙና ኪይሙኒን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማቋረጥ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ የሰበታዎችን የማንሰራራት ጉዞ ፈተና ውስጥ አስገብቶታል።
ይባስ ብሎ ወልዋሎዎች ሳይጠበቅ በ56ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ኢታሙና በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ለሰመረ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ወጣቱ ሰመረ ሃፍታይ በግሩም አጨራረስ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ማሳደግ ችሏል።
በደቂቃዎች ልዩነት የሰበታዎችን ተስፋ ያለመለለመች ግብ ምስጋናው ዮሐንስና በወልዋሎ ግብጠባቂ አለመናበብ ምስጋናው ወደ ኃላ የመለሰውን ኳስ ሳይጠበቅ ከመረብ ላይ አርፋ የግብ ልዩነቱ ወደ አንድ ሊጠብ ችሏል።
በቀሩት ደቂቃዎች ወልዋሎች በከፍተኛ ጥንቃቄ በእጃቸው የገባውን ሶስት ነጥብ ለማስጠበቅ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል። በተጨማሪ ደቂቃም መሐል ሜዳ ላይ የሰበታ ተጫዋቾች የሰሩትን የቅብብሎ ስህተት ተጠቅሞ ተስፈኛው ሰመረ ሃፍታይ ሰለሞን ደምሴ የግብ ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተክትሎ በተረጋጋ አጨራረስ የቡድኑን መሪነት ወደ ሦስት በማሳደግ ክለቡ በመጀመሪያው ሳምንት ከሜዳው ውጭ ጣፋጭ ሶሶት ነጥብ እንዲያሳካ አስችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ