ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ሲዳማ ቡናን በመርታት ዓመቱን በድል ጀመረ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2012 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ እጅግ አስደሳች የደጋፊዎች መልካም ተግባራት የታዩበት የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በባለሜዳው ወላይታ ድቻ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባለፈው ዓመት ከስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ጋር በተገናኘ የእርስ በእርስ ጨዋታቸውን በገለልተኛ ሜዳ ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮ በተሰሩ የደጋፊዎች መልካም ግንኙነት ሥራዎች እጅጉን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ጨዋታቸውን ጀምረው ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ ከዛሬው ጨዋታ ቀደም ብሎም እንኳን በሰላም መጣችሁ የሚል መልዕክት ያዘለ እንዲሁም እኛ ወንድማማቾች ነን በሚል በሁለቱም ደጋፊዎች የተዘጋጀ የባነር ልውውጥ ተከናውኗል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ አዲስ በክረምቱ ያዘዋወሯቸውን ተጫዋቾችን ተጠቅመዋል፡፡ ባለ ሜዳው ወላይታ ድቻ መክብብ ደገፉ፣ ነጋሽ ታደሰ እና ኢድሪስ ሰዒድን፤ ሲዳማ ቡና ደግሞ ጊት ጋትኮች እና ብርሀኑ አሻሞን ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት አስገብተዋል፡፡

ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በጥሩ ዳኝነት መርቶ ባጠናቀቀው እንዲሁም ፍፁም ለጨዋታ ምቹ ባልነበረው የሶዶ ስታዲየም የተደረገው ጨዋታ ወላይታ ድቻ በተደራጀ የመሀል ሜዳ አጨዋወት እና በጥሩ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ የቻሉበት፤ ሲዳማ ቡናዎች ወደ አዲስ ግደይ በረጅሙ ከሚጣሉ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት የነበረ ቢሆንም ጠጣሩን የጦና ንቦች የመከላከል ሂደት አስከፍቶ ለመግባት በጉልህ ሲቸገሩ ተመልክተናል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በመሀል ሜዳ ላይ በነጋሽ ታደሰ እና እድሪስ ሰይድ አስደናቂ ጥምረት የተዋቀረው የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራው ቡድን ተዳክሞ በታየው የሲዳማ ቡና ላይ ብልጫ ማሳየት ቢችልም የሲዳማን የግብ ክልል ሰብሮ ለመግባት ግን ጊዜ ፈጅቶባቸዋል። 14ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ በቀኝ በኩል በግንባር የሰጠውን ሀብታሙ ገዛኸኝ ሳይጠቀምበት የቀረውም ሲዳማ ቡናዎችን ቀዳሚ ያሰኘች ሙከራ ነበረች፡፡

ድቻዎች 20ኛ ደቂቃ ዘላለም ኢያሱ ከቀኝ መስመር የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ያሳለፈለትን ኳስ እዮብ ዓለማየሁ በቀጥታ መቶ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ አድኖበታል፡፡ በማጥቃቱ ቀዝቀዝ ብለው ነገር ግን የመልሶ ማጥቃት ከግብ ጠባቂ በረጅሙ በሚለጉ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ባሰቡት ሲዳማ ቡናዎች በኩል ሀብታሙ ገዛኸኝ በረጅሙ ከአበባየው ዮሀንስ እግር ስር በረጅሙ ያገኛት ዕድል በቀላሉ ወደ ግብ ክልል ይዞ ገብቶ ያመከናት መልካም አጋጣሚ ነበረች፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ሲዳማ ቡና አስቀድሞ በመጀመሪያ አጋማሽ የተወሰደባቸውን የመሀል ሜዳ ብልጫ ለመቆጣጠር ያለመ ቅያሬን አድርገዋል። አበባየው ዮሀንስን በዳዊት ተፈራ፤ ዮሴፍ ዮሀንስን በሚካኤል ሀሲሳ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ ሆኖም አጋማሹ ከጀመረ ከሶስት ደቂቃዎች ማለትም 48ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ዓመት ያህል በጉዳት ከሜዳ ርቆ የተመለሰው አማካዩ ዘላለም ኢያሱ በቀኝ በኩል መሬት ለመሬት ያቀበለውን ኳስ የሲዳማ ቡና የተከላካይ ክፍል መዘናጋትን ተጠቅሞ ባዬ ገዛኸኝ ከመሀል ሾልኮ በመውጣት ግብ አስቆጥሮ የጦና ንቦቹን ቀዳሚ አድርጓል፡፡

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ በመጠኑም ቢሆንም ቀይረው ባስገባቸው ሚካኤል እና ዳዊት አማካኝነት ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሞከሩት ሲዳማ ቡናዎች ከሁለቱ አማካዮች በሚመነጩ ዕድሎችን ለማግኘት ጥረቶችን አድርገዋል። ሀብታሙ ገዛኸኝ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ አሁንም አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ሲዳማዎችን ወደ ጨዋታ ልትመልስ የምትችል ሙከራ ነበረች፡፡

የመጨረሻዎቹን 20 ደቂቃዎች ድቻዎች መልካም የግብ ማስቆጠር አጋጣሚዎት ቢያገኙም በእለቱ በርካታ ኳሶችን ሲያመክን የነበረው የሲዳማ ቡና ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ ግብ ከመሆን አድኗቸዋል፡፡ ከሀዋሳ ከተማ ድቻን በክረምቱ የተቀላቀለውና በዛሬው ጨዋታ ድንቅ ጊዜ የነበረው ነጋሽ ታደሰ ሁለት ጊዜ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ በአስደናቂ ሁኔታ ያወጣበት ክስተት ግብ ጠባቂው ከተመልካቾች አድናቆትን እንዲያገኝ ያስቻለው ነበር።

81ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች መሪነታቸውን አስተማማኝ ያደረገች ግብ አስቆጥረዋል። ከነቀምቴ ከተማ ቡድኑን የተቀላቀለው ዳንኤል ዳዊት የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ግብ ክልል ያሻገረለትን ኳስ ከወሎ ኮሞቦልቻ አዲስ ፈራሚው እድሪስ ሰዒድ አስቆጥሯል፡፡

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና ወደ ጨዋታ ለመመለስ በይገዙ ቦጋለ አማካኝነት አጋጣሚን አግኝቶ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ወላይታ ድቻም 2ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል፡፡

ጨዋታው አንድም ቢጫ ካርድ ሳይመዘዝበት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ