የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከጀመረባቸው የዛሬ ጨዋታዎች መካከል በሼር ሜዳ የተደረገው የወልቂጤ እና የጊዮርጊስ ጨዋታ ምንም ግብ ሳይታይበት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።

“የዛሬው ውጤት እኛን አይገልፀንም” ደግያረጋል ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

“ዛሬ የገጠምነው በሊጉ በእጅጉ ልምድ ያለውን ቡድን ነው። በተቃራኒው እኛ ለሊጉ አዲስ ነን። ነገር ግን ሜዳ ላይ የነበረው ተገላቢጦሽ ነው። በእግር ኳስ ማሸነፍ ፤ መሸነፍ ወይም አቻ መሆን ያለ ነው ። የዛሬው ውጤት እኛን አይገልፀንም። ምክንያቱም በመጀመሪያውም ሆነ ሁለተኛው አጋማሽ ወደ ግብ ክልል በመድረስ እኛ የተሻልን ነበርን። በእውነት በልጆቼ እጅጉን ተደስቻለው። ሦስት ነጥብ ለማምጣት ያቅማቸውን ጥረዋል። በሚቀጥለው ጨዋታ ከዚህ ተሽለን እንመጣለን።”

“አሁን የምናስበው ስለሚቀጥለው ጨዋታችን ነው” ሰርዳን ዢቮጅሆቭ (ሰርጂዮ) – ቅዱስ ጊዮርጊስ

” ጨዋታው ፈጣን እና ቆንጆ ነበር ፤ እናሽንፍለን ብለን ነበር የጠብቅነውም። ምክንያቱም በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ ወልቂጤን አሸንፈነው ነበር ፤ ቡድኑም ራሱ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ተቀዛቅዘን ነበር። ምክንያቱን ከዚህ በኋላ ከተጫውቾቼ ጋር በጋራ የምናየው ነው የሚሆነው። በሁለተኛው አጋማሽ ግን የግብ ዕድሎች ብንፈጥርም ያገኘነውን የግብ አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻልንም። ይህ የመጀመሪያው ጨዋታችን ነው። ማሸነፍ ነበር የምንፈልገው ፤ ያለምንም ግብ ተጠናቋል። አሁን የምናስበው ስለሚቀጥለው ጨዋታችን ነው። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ