ሪፖርት | የጅማ አባ ጅፋር እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

ከዐምናው በተሻገረ ቅጣት ከሜዳቸው ውጭ ለመጫወት ተገደው በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ጅማ አባ ጅፋሮች ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

በስታድየሙ ከነበረው ተመልካች ቁጥር እጅግ ከማነሱ በቀር ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የጨዋታው እንቅስቃሴ አድርገው በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ እየተመራ ያለ ጎል ተጠናቋል።

የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ያልተሟሉላቸው ጅማ አባ ጅፋሮች በመጀመርያው አጋማሽ ከባህር ዳር በእጅጉኑ ተሽለው መንቀሳቀስ ችለዋል። ያም ቢሆን ቡድኑ ውስጥ ከአማካይ ተጫዋቾች ኳስ በመቀበል አደራጅቶ ጎል የሚያስቆጥር፣ እና የጎል አጋጣሚዎችን መፍጠር የሚችል ሁነኛ የፊት መስመር ተጫዋች ባለመኖሩ ግልፅ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ተቸግረው ታዩ እንጂ እንደ ባህር ዳር መዳከም ጎል ማስቆጠር በቻሉ ነበር።

የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጨዋታውን አንብቦ ከጨዋታ ውጭ እንቅስቃሴ በመመልከት የሚያቀብል ተጫዋች በመጥፋቱ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም እንቅስቃሴ በዝቶ ነበር። እንዲሁም የኳስ ቅብብሎች ብዙም ሳይቆይ የሚቆራረጥበት እና ከማዕዘን ምት በሚሻገሩ ኳሶች የጎል ዕድል ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት በተደጋጋሚ ተመልክተናል።

ባህር ዳሮች ወደ ጨዋታው በፍጥነት ለመግባት ጊዜ ወስዶባቸው ከ34ኛው ደቂቃ በኃላ በመነቃቃት የጎል ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ቡድኑን ዘንድሮ የተቀላቀለው ተስፈኛው ወጣት ሳሙኤል በግራ መስመር ቆርጦ በፍጥነት በመግባት ያሻገረውን ወሰኑ ዓሊ በጥሩ ሁኔታ ኳሱን ተቆጣጥሮ ለማማዱ ሲዲቤ አምስት ከሃምሳ ውስጥ አቀብሎት ማሊያዊው አጥቂ በቮሊ መትቶ ለጥቂት በግቡ አናት ወጥቶበታል።

ባህር ዳሮች ጥረታቸው ቀጥሎ ብዙም ሳይቆዩ 37ኛው ደቂቃ ላይ በፍጥነት በአንድ ሁለት ቅብብል በዕለቱ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው ዜናው ፈረደ ከግራ መስመር በጥሩ ሁኔታ ተከላካዮችን በማለፍ ሳጥን ውስጥ ገብቶ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ እንደምንም ያዳነበት፤ በተጨማሪም 39ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ተስፋዬ ሳይጠበቅ ያሻግረዋል የተባለውን ኳስ በቀጥታ ወደ ጎል መቶት በተመሳሳይ ግብጠባቂው ሰዒድ እንደምንም ለመያዝ ሲሞክር የተፋውን በኳሱ በቅርብ ርቀት የነበረው ዜናው ፈረደ እንዳይጠቀምበት የአባጅፋር ተከላካዮቹ ወደ ውጭ ያራቁበት ለጣና ሞገዶቹ መልካም አጋጣሚዎች ነበሩ።

በጅማ አባ ጅፋር በኩል የቀድሞ ክለቡን የገጠመው ኤልያስ አሕመድ ለቡድኑ ተጫዋቾች ኳሱን በማደራጀት እንዲሁም በግሉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አስገራሚ ነበር። ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ ለአባጅፋሮች የሚያስቆጭ ጎል መሆን የሚችል ዕድል 43ኛው ደቂቃ ጀሚል ያዕቆብ በቀኝ መስመር በቀጥታ ሳጥን ውስጥ በመግባት ወደ ጎል የመታውን ግብጠባቂው ሀሪሰን ሄሱ ሲተፋው ለጎሉ ሁለት ሜትር ርቀት ላይ የነበረው ተመስገን ደረሰ አገባው ሲባል የጣና ሞገዶቹ አምበል ፍቅረሚካኤል እንደምንም በመንሸራተት ተደርቦ ያወጣበት ለአባ ጅፋሮች መልካም የጎል አጋጣሚ ሆኖ ጨዋታውም ወደ እረፍት ያለ ጎል አምርቷል።

ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ በሁለተኛው አጋማሽ ድምክመታቸውን በሚገባ ቀርፈው የመጡት ባህር ዳሮች በሁለቱም መስመሮች በፍጥነት ወደ ጎል ቢደርሱም ጎል መሆን የሚችሉ ዕድሎችን አምክነዋል። በ48ኛው ደቂቃ ወሰኑ ቀኝ መስመር በፍጥነት ገብቶ ተከላካይ በማሸማቀቅ ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ፍፁም ዓለሙ አቀብሎት፤ ፍፁም ደግሞ በጥሩ መንገድ ጎል አጠገብ ብቻውን ለሚገኘው ማማዱ ሲዲቤ ቢያቀብለውም ሲዴቤ ተሸራቶ ኳሱን ደገፍ ለማድረግ ቢሞክርም በመርዘሙ ሳያገኛት የቀረው እንዲሁም ከተሻጋሪ ኳስ ማማዱ ሲዲቤ በግንባሩ ሞክሮ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወደ ውጭ የወጣበት ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ነበሩ።

የባህር ዳሮችን ብልጫ ለመቆጣጠር የተቸገሩት አባ ጅፋሮች በ63ኛው ደቂቃ ጥሩ የጎል እድል መፍጠር ችለው ነበር። ተቀይሮ የገባው እና ከተለመደው ቦታው በተለየ የፊት አጥቂ ሆኖ የተጫወተው አምረላ ደልታታ ከመሐል ሜዳ ኤርሚያስ የጣለለትን ኳስ ከተከላካዮች ፈጥኖ በመሮጥ ቢደርስም ሚዛኑን ባለ መጠበቁ ምክንያት ኳሱ በእግሩ ስር በመሹለኳ ለግብጠባቂው ሲሳይ ሆናለች።

ባህር ዳሮች ጎል ፍለጋ ኤልያስ አታሮ በሚገኝበት የግራ የሜዳ ክፍል የነበረውን ክፍተት ለመጠቀም በተደጋሚ ወሰኑ ዓሊ እና ፍፁም ዓለሙ የሚያደርጓቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ 68ኛ ደቂቃ በጎል የታጀበ ለማድረግ ተቃርበው ነበር። ሆኖም ፍፁም ዓለሙ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው ሰዒድ አድኖበታል። 75ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማው ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ አዳማ ሲሶኮ በግራ እግሩ ወደ ጎል ቢመታውም ለጥቂት ወደ ውጭ ሲወጣበት ዜናው ፈረደ በጥሩ ሁኔታ ተከላካዮችን ቆርጦ ሳጥን ውስጥ ገብቶ በመምታት ብዙዎች ደጋፊዎች እና ተቀያሪ ወንበር ላይ ያሉትን ተጫዋቾች ሳይቀር ጎል መስሎ ያስጨፈረው ሙከራ የውጪውን መረቡን ነክቶ ወጥቷል።

በ88ኛው ደቂቃ ማማዱ ሲዲቤ በአንድ ሁለት ቅብብል የተቀበለውን ኳስ ተከላካዮችን በማለፍ ለጎል አመቻችቶ ቢመታውም የአባ ጅፋር ተከላካዮች የሞት ሞታቸውን ያጨናገፉት ባህር ዳሮች ለጎል እጅጉኑ የቀረቡበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

በተጨማሪ ደቂቃ ለአባጅፋሮች ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት በአስጨናቂ ሁኔታ ሱራፌል ዐወል ወደ ጎል የመታውን ግብጠባቂው ሀሪሰን በሚገርም ብቃት አድኖበት ጨዋታው በርካታ ሙከራ እንጂ ጎል ሳያስመለክተን በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ