ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2012 የውድድር ዘመን ባሳለፍነው እሁድ እና ሰኞ በተደረጉ ስምንት የአንደኛ ሳምንት ጨዋታዎች ጅማሮውን አድርጓል። የሳምንቱ ቅድመ ዳሰሳ፣ ቀጥታ ስርጭት፣ መረጃዎች፣ ሪፖርት፣ አስተያየቶች እና ቃለመጠይቆች ያቀረበችላችሁ ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ የሳምንቱን ምርጥ 11 በዚህ መልኩ አሰናድታለች።

* የሳምንቱ ምርጥ 11 ምርጫ የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች በተመለከቷቸው ጨዋታዎች ላይ ለተጫዋቾቹ በሰጡት የተናጠል ነጥብ ላይ የተመረኮዘ ነው።


ግብ ጠባቂ – መሳይ አያኖ – ሲዳማ ቡና

በመጀመሪያ ሳምንት ሲዳማ ቡና ምንም እንኳን በወላይታ ድቻ ሁለት ለባዶ ቢሸነፍም መሳይ በግሉ በርከት ያሉ ለግብ የቀረቡ ኳሶችን አምክኗል። እንደ ግብ ጠባቂው አቋም ሆኖ እንጂ ውጤቱ ከዚህም በከፋ ነበር። ዓምና በተወሰኑ ጨዋታዎች ቡድኑን ዋጋ ያስከፈሉ ስህተቶች ቢሰራም አዲሱን የውድድር ዘመን በጥሩ ብቃት መጀመር ችሏል።

ቀኝ ተከላካይ – አሸናፊ ሀፍቱ (መቐለ 70 እንደርታ)

በተክለ ሰውነቱ ደቀቅ ያለው አሸናፊ ቡድኑ መቐለ ሆሳዕናን 2ለ1 በረታበት ጨዋታ ጥሩ ብቃቱን አሳይቷል። ዐምና እምብዛም የመሰለፍ እድል ያላገኘው አሸናፊ በተለይ የሥዩም ተስፋዬ ቅጣት ላይ መሆኑን ተከትሎ በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ እንዲሁም በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግ ችሏል። በሆሳዕናው ጨዋታ ላይም ያሬድ ከበደ ላስቆጠራት ግብ ከፍተኛ ሚና ተወጥቷል።

መሐል ተከላካይ – አቼምፖንግ አሞስ (ወልዋሎ)

ያሳለፍነው የውድድር ዘመን በጉዳትና በተለያዩ ምክንያቶች ከውድድር ርቆ የነበረው አሞስ ዘንድሮ የቀደመ ሥሙን ለመመለስ ጠንክሮ እየሰራ እንደሚገኝ በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ የነበረው ቆይታ ምስክር ነው። በአማካይና በተከላካይነት መጫወት የሚችለው አሞስ በመክፈቻው ጨዋታ ቡድኑ ሰበታን ሲረታ በተለይ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች የሚቀመስ አልነበረም።

መሐል ተከላካይ – አሚን ነስሩ (መቐለ 70 እንደርታ)

ዐምና ምዓም አናብስት እስከ ሻምፒየንነት በዘለቀው ጠንካራ የሊጉ ጉዟቸው ላይ የጀርባ አጥንት የነበረው አሚን በእሁዱ የሆሳዕና ጨዋታ ከላውረስ ኤድዋርድ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር ግዙፉቹን የሆሳዕና ተጫዋቾች በማቆምም ሆነ ወሳኝ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በማቋረጡ ረገድ ስኬታማ ነበር።

ግራ ተከላካይ – ረመዳን ዩሱፍ (ስሑል ሽረ)

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ ተመራጭ የግራ መስመር ተከላካይ የሆነው ረመዳን ትላንት ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን 1ለ0 በረታበት ጨዋታ የጎላ የማጥቃት ተሳትፎ ነበረው። በጨዋታው ሽረዎች ያደረጓቸው አብዛኞቹ የግብ ሙከራዎችም መነሻ የነበሩት ከእሱ እግር ስር የተነሱ ነበሩ።

አማካይ – ኤልያስ አህመድ (ጅማ አባ ጅፋር)

የቀድሞ አሰልጣኙን ተከትሎ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ያመራው ኤልያስ የቀድሞ ክለቡን በገጠመበት በትላንቱ ጨዋታ በተለይ አባ ጅፋሮች የተሻሉ በነበሩት የመጀመሪያ አጋማሽ ቡድኑ በፊት መስመር ውጤታማ የማጥቃት ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾችን አለመያዙ እንጂ በርካታ ኳስች በማደራጀትም ሆነ ጥሩ ጥሩ የማጥቃት አጋጣሚዎችን የሚፈጥሩ ኳሶችን ወደፊት በማሳለፍ ውጤታማ ቀንን በግሉ ማሳለፍ ችሏል።

አማካይ – አዳነ ግርማ (ወልቂጤ ከተማ)

ወልቂጤ ከተማን በረዳት አሰልጣኝ ተጫዋቾችነት ለማገልገል የተቀላቀለው አዳነ ግርማ ሼር ሜዳ ላይ ተቀይሮ ከሜዳ እስከወጣበት ደቂቃ ድረስ ወልቂጤ ከተማን በመከላከል እንዲሁም ማጥቃቱን በሚዛናዊነት በመከወን ለቡድኑ ከፍተኛ ግልጋሎት ሰጥቷል። አዳነ በጨዋታውም የተነጠሉትን የቡድኑ አጥቂዎች ከተቀረው ቡድን ጋር ለማገናኘት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።

ቀኝ መስመር አጥቂ – ሠመረ ሃፍታይ (ወልዋሎ)

ተስፈኛው ወጣት ሰመረ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት ቡድኑ ሰበታ ከተማን እንዲያሸነፍ የረዱ ወሳኝ ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። በመስመርና በፊት አጥቂነት መጫወት የሚችለው ሠመረ ሁለቱን ግቦች ሲያስቆጥር የነበረው መረጋጋትና በራስ መተማመን ሌሎች በእሱ ዕድሜ ለሚገኙ ተጫዋች ተምሳሌት የሚሆን ነው።

አጥቂ አማካይ – ያሬድ ከበደ (መቐለ 70 እንደርታ)

በሰሞኑ ጨዋታዎች መቐለ 70 እንደርታን በአምበልነት እየመራ የሚገኘው ያሬድ መቐለ ሆሳዕናን ሲረታ የመጀመሪያውን ግብ ማስቆጠር ሲችል በጨዋታውም ቡድኑ ተጨማሪ ግቦችን እንዲያስቆጥር ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል።

ግራ መስመር አጥቂ – ዜናው ፈረደ (ባህር ዳር ከተማ)

ከመስመር እየተነሳ ተጫዋችን ለማለፍ የማይቸገረው ዜናው በጅማው ጨዋታ ላይ በበርካታ አጋጣሚዎች ከግራ መስመር ተጫዋቾችን እያታለለ ወደ ሳጥን በመድረስ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል። እንደአዲስ በተገነባው ባህር ዳር ከተማ ስብስብ ውስጥ ዘንድሮ የተሻለ ጊዜ ያሳልፋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

አጥቂ – ባዬ ገዛኸኝ (ወላይታ ድቻ)

በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ሲዳማ ቡናን 2ለ0 ሲረታ ባዬ ገዛኸኝ የሲዳማን ተከላካዮች መዘናጋት በመጠቀም ግብ ከማስቆጠር አልፎ በሁለቱም አጋማሾች የሲዳማ ቡና ተከላካዮች ከኳስ ጋር እንዲሁም ያለ ኳስ ባለው ተገማች ያልሆነ እንቅስቃሴ ሲያስቸግር ውሏል።


ሌሎች ሊጠቀሱ የሚገባቸው ተጫዋቾች

በሳምንቱ ምርጥ 11 ካልተካተቱ ነገር ግን በየጨዋታዎቹ መልካም አቋም ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል የፍፁም ቅጣት ምት ከማዳን በተጨማሪ (ምንም እንኳን የተመለሰው ኳስ ወደ ጎልነት ቢለወጥም) በርካታ ጎል የሚሆኑ ኳሶች ያመከነው የድሬዳዋ ከተማው ፍሬው ጌታሁን፣ ሀዲያ ሆሳዕና በመቐለ በተሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛዋን የሆሳዕና ጎል ያስቆጠረው ተከላካዩ ደስታ ጊቻሞ፣ የቡድኖቻቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ሚና የነበራቸው አማካዮቹ ፍፁም ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ) እና ኤልያስ ማሞ (ድሬዳዋ ከተማ)፣ ወላይታ ድቻ ሲዳማ ቡናን ባሸነፈበት ጨዋታ ምርጥ እንቅስቃሴ ያሳየው ነጋሽ ታደሰ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን እንዲያሸንፍ ጉልህ ሚና የተወጡት ብሩክ በየነ እና መስፍን ታፈሰ ይጠቀሳሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ