የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ድልድል ወጥቷል

ቱኒዚያ እንደምታስተናግደው በሚጠበቀው የ2020 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የሚደረገው የማጣርያ ውድድር ድልድል ሲወጣ ኢትዮጵያ ከጎረቤቷ ጅቡቲ ጋር ተደልድላለች።

የተሳታፊዎችን ቁጥር ጨምሮ ለመጀመርያ ጊዜ በ12 ሀገራት መካከል ይካሄዳል የተባለው ይህ ውድድርን ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ለማስተናገድ ዕድሉ ተሰጥቷት የነበረ ቢሆንም በቂ ዝግጅት ባለማድረጓ መብቱን ተነጥቃለች። ከተሳታፊዎች ቁጥር በተጨማሪ በማጣርያው የሚሳተፉ ሀገራት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው ውድድሩ በ36 ሀገራት መካከል ከመጋቢት ወር ጀምሮ ይከናወናል።

ካፍ እስካሁን ድልድሉን ይፋ ባያደርግም ጎል ዶት ኮምን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መገናኛ ብዙሀን እንዳወጡት መረጃ ከሆነ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር በመጀመርያው ማጣርያ የተደለደለች ሲሆን ከመጋቢት 26-28 የመጀመርያ ጨዋታዋን፣ ከሚያዝያ 6-8 ደግሞ የመልስ ጨዋታዋን ታደርጋለች። ይህን ዙር በድል ከተወጣችም በመጨረሻው ዙር ሞሮኮን የምትገጥም ይሆናል። ከሰኔ 23-25 መጀመርያ ጨዋታ የሚደረግበት ሲሆን ከሰኔ 30-ሐምሌ 2 የመልስ ጨዋታ የሚከናወን ይሆናል።

በተያያዘ ከ17 ዓመት በታች የዓለም የሴቶች ዋንጫ በህንድ አዘጋጅነት በቀጣዩ ዓመት ሲደረግ ሶስት ዙር በሚኖረው በዚህ ማጣርያ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ዙር ከዩጋንዳ ጋር ተደልድላለች፡፡ ጥር ወር ላይ የሚደረገውን ማጣርያ በድል የተወጣው ሀገር በቀጣይ ዙር ከታንዛንያ እና ቡሩንዲ አሸናፊ ጋር ሚያዝያ ወር ላይ ይጫወታል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በጆርዳን እና ዩራጓይ በተስተናገዱት የ2016 እና 2018 ውድድር ማጣርያዎች ላይ መሳተፏ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ