የካፍ ፕሬዝዳንት እና የፊፋ ፀሀፊ ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ጋር ውይይት አድርገዋል

ኢትዮጵያ በምታሰናዳው የፊፋ ዓመታዊ ስብሰባ ቅድመ ዝግጅት ዙርያ የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ እና የፊፋ ዋና ፀሀፊ ፋትማ ሳሞራ ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ትላንት ከሰአት ውይይት አድርገዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የፊፋ 69ኛው አመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በፈረንሳይ ፓሪስ ሲደረግ ኢትዮጵያ ቀጣዩን 70ኛውን ስብሰባ እንድታዘጋጅ መመረጧ ይታወሳል፡፡ ለዚህ ጉባዔ ኢትዮጵያ ከአሁኑ ወደ ቅድመ ዝግጅቷ የገባች ሲሆን ይህ ዝግጅት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለውን ለመታዘብ እና መሰናዳት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር ከትላንት በስቲያ የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ እንዲሁም የፊፋ ዋና ፀሀፊ ፋትማ ሳሞራ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውንን ዘግበናል፡፡ ሁለቱ የእግር ኳሱ መሪዎች ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጅራ ጋር በጋራ በመሆን ከሰዓት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቢሮ በመገኘት ውይይቶችን አድርገዋል፡፡

በውይይታቸው በአብዛኛው በጉባዔው ተሳታፊ ለሚሆኑ አካላት ከተዘጋጀው የማረፊያ ስፍራ አንስቶ እስከ ጥበቃ ድረስ እየተደረገ ስላለው ዝግጅት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ከፕሬዚዳንቷ ጋር በጋራ በመሆን ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅም ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማሰናዳቷ ለዚህም ጉባዔ መሳካት አስተዋጽኦ ስላለው ጉባኤውን በሙሉ ኃላፊነት እስከ ፍፃሜው ድረስ ለማስፈፀም ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ቆይታቸው የተሳካ እንዲሆን መመኘታቸውንም ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በነሀሴ ወር የፊፋ ሰባት ያህል ተወካዮች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሆቴሎች እና የአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሾችን የጥራት ፍተሻ ያደረጉ ሲሆን አስር ያህል ዘመናዊ ሆቴሎች ዝርዝር በመውሰድ ማምራታቸው ይታወሳል። ይህንንም ሂደት የፊፋ ፀሀፊ በዝርዝር ለፕሬዝዳንቷ አስረድተዋል፡፡ ሁለቱ የእግር ኳስ መሪዎች ውይይታቸውን ካጠናቀቁ በኃላ ትላንት በዛኑ ቀን ማምሻውን ተመልሰዋል፡፡

የፊፋ 70ኛ ዓመታዊ ጉባዔ በግንቦት ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ ይሰናዳል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ