” ነፃ ሆኜ ወደ ሜዳ ስለገባሁ ነው የምችለውን ያህል ያደረግኩት” መሳይ አያኖ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውጪ ግብ ጠባቂዎችን ከማይጠቀሙ ክለቦች መካከል አንዱ ነው፤ ሲዳማ ቡና። ክለቡ ባለፈው ዓመት ስኬታማ የውድድር ጊዜ እንዲኖረው ከረዱ ተጫዋቾች መካከል ደግሞ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ይጠቀሳል፡፡ ተጫዋቹ በሀላባ ፣ አርባምንጭ ፣ ደቡብ ፖሊስ እና ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ በሲዳማ ቡና መልካም የውድድር ዓመታትን አሳልፏል፡፡ 

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዕሁድ ጅማሮን ሲያደርግ ሲዳማ ቡና ምንም እንኳን በወላይታ ድቻ ከሜዳው ውጪ 2-0 ቢረታም መሣይ በግሉ በጨዋታው በርካታ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማምከን ከተመልካቹ አድናቆት ተችሮት ተመልክተናል፡፡ ግብ ጠባቂው በወቅቱ ስለነበረው ጨዋታ እንዲሁም ስለ ዕቅዶቹ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡

በመጀመሪያው ሳምንት ቡድናችሁ ከወላይታ ድቻ ጋር ስለነበረው ጨዋታ በማውራት እንጀምር…

“በጣም አሪፍ ነበር አጀማመሩ። ሁለቱ ክለቦች የነበረባቸው የፀጥታ ችግር ተቀርፎ በፍቅር ተቀይሮ በተለየ ስሜት ነው ያገኘሁት። ወደ ጨዋታው ስገባ ሜዳው የነሱም አሰልጣኝ እንደገለፀው ለጨዋታ ምቹ አልነበረም ፤ ለኛም አስቸጋሪ ሆኖብናል። ውጤትም እንድናጣ ያደረገን ይሄው ነው። ውጤቱ እንደመጀመሪያ ጨዋታ ብዙም የከፋ አይደለም። ምክንያቱም ቡድናችን በወጣቶች የተገነባ ነው ፤ በቶሎ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ተነጋግረን እየሰራን ነው።”

ቡድናችሁ በጨዋታው ቢሸነፍም አንተ ግን በግልህ በርካታ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን ስታመክን አይተናል። ያሳየኸው የተለየ ወቅታዊ ብቃት ከምን የመጣ ነው ?

“የተለየ ነገር የለውም። በእርግጥ በ2011 የነበረብኝን ድክመት ቀርፌ ዘንድሮ ብቁ ሆኖ ለመገኘት ብዙ ዝግጅቶችን አድርጊያለሁ። ሁለተኛ ወደ ሶዶ በምንሄድበት ወቅት እኔ ውስጥ ምንም አልነበረም። ብዙ ጎደኞቼ ውስጥ ግን ፍርሀት ነበር። ማለቴ ባለው ነገር ጭንቅላታቸው ተረብሾም ነበር። እኔ ውስጥ ደግሞ በጭራሽ ይሄ ነገር አልነበረም። ጥሩ አቀባበል እንደሚኖር ውስጤ አምኖ ነበር፡፡ ከዛ አንፃር ነፃ ሆኜ ወደ ሜዳ ስለገባሁ ነው የምችለውን ያህል ያደረኩት። ቡድኔን ይዤ ለመውጣት ሞክሬያለሁ ተጋጣሚያችን ብልጫ ስለነበረው ባይሳካም።”

እንደዓምናው ሁሉ ዘንድሮም ለዋንጫው እንፎካከራለን ብለህ ታምናለህ ?

“ያለፈው ዓመት አሪፍ ጊዜን አሳልፈናል። በአንድ ነጥብ ተበልጠን ነው ዋንጫ ያጣነው። ዘንድሮም በርካታም ባይሆኑ አዳዲስ ተጫዋቾች ተቀላቅለውናል። በፍጥነትም ከቡድኑ ጋር ተዋህደዋል። በመሆኑም ዘንድሮም ቡድናችን ጠንካራ ነው። በሽንፈት ብንጀምርም በአንድ ጨዋታ ብቻ አይለካም ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተሻሻልን ካለፈው ዓመት የተሻለ ነገር እንሰራለን ብዬ አምናለሁ፡፡”

ቀጣይ ዕቅድህ ምን ይሆን ?

“ዕቅዴ በመጀመሪያ ሀገሬን ወክዬ መጫወት ነው። ሲቀጥል ደግሞ እግዚአብሔር ከፈቀደው ከሀገር ውጪ ወጥቼ ለመጫወት ግንኙነት ማድረግ ጀምሪያለሁ። ለምን እኛ ወጥተን መጫወት አንችልም ? እንችላለን ! ያው እንዳየኸውም በመጀመሪያው ጨዋታ ላይ ጥሩ ነበርኩ። ይሄን ማስቀጠል እና በዋናነት ግን ሀገሬን ወክዬ መጫወትን እፈልጋለሁ ለዛም ጠንክሬ መስራት ጀምሬያለሁ፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ