ኢትዮጵያ በሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጋጣሚዋን አውቃለች

በሴፕቴምበር 2020 ለሚከናወነው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ለማለፍ የማጣርያ ጨዋታዎች ከወራት በኋላ መካሄድ ሲጀምሩ ኢትዮጵያም የቅድመ ማጣርያው ተጋጣሚዋን አውቃለች፡፡

በ16 ሀገራት መካከል ለሚደረገው ውድድር ከአፍሪካ ሁለት ሀገራት የሚያልፉ ሲሆን አራት የማጣርያ ዙሮችን (ከቅድመ ማጣርያ እስከ 3ኛው ዙር) አቅፏል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ከቡሩንዲ ጋር በቅድመ ማጣርያው ስትደለደል የመጀመርያ ጨዋታዋን ከጥር 8-10 ከሜዳዋ ውጪ፤ የመልስ ጨዋታዋን ደግሞ ከጥር 22-24 በሜዳዋ ታከናውናለች።

ኢትዮጵያ ይህን የማጣርያ ዙር ካለፈች በመጋቢት ወር ከዚምባብዌ እና ማላዊ አሸናፊ ጋር በአንደኛ ዙር ማጣርያ የምትፋለም ይሆናል።

አስተናጋጁ ሀገር እስካሁን ያልተለየበት የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ በመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ይፋ ይደረጋል። ፓናማ እና ኮስታሪካ (በጋራ) እንዲሁም ናይጄርያ ውድድሩን ለማስተናገድ የመጨረሻዎቹ እጩ የሆኑ ሀገራትም ናቸው።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በ2016 ፓፓዋ ኒው ጊኒ ላይ ለተሰናዳው ውድድር ለማለፍ ተቃርባ በመጨረሻ ዙር በጋና ተሸንፋ ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ