በዚህ ሳምንት ከሚደረጉት ጨዋታዎች ተጠባቂ የሆነው የጣና ሞገዶቹ እና ምዓም አናብስትን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በመጀመርያው ጨዋታ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ነጥብ የተጋሩት ባህር ዳር ከተማዎች ከዓምናው አጨዋወታቸው አንፃር መጠነኛ ለውጥ አድርገው ነው ወደ ውድድር የተመለሱት። የጣና ሞገዶቹ ባለፈው የውድድር ዓመት በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እየተመሩ በፈጣን የመስመር ሽግግሮች ሲጫወሩ የነበረ ሲሆን አሁን በአዲሱ አሰልጣኝ እየተመሩ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚጥር ቡድን ገንብተዋል። በተለይ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ያሏቸውን የአማካይ መስመር አማራጮች በመጠቀም ተጋጣሚ ላይ ብልጫ ለመውሰድ ሲጥሩ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ታይቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እና በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ በሦስቱም የሜዳ ክፍሎች ላይ በቋሚነት ሲጫወቱ የነበሩት አዳማ ሲሶኮ፣ ፍፁም ዓለሙ እና ማማዱ ሲዲቤ በነገውም ጨዋታ ለቡድኑ ልዩነት ፈጣሪ ተጨዋቾች ይሆናሉ ተብሎ ሲጠበቅ አዳማ ላይ ጅማ አባጅፋርን ከገጠመው ስብስብ ቡድኑ ነገ ለውጦችን ያደርጋል ተብሎ ባይጠበቅም ምናልባት አሰልጣኙ የግርማ ዲሳሳን ግልጋሎት ለማግኘት መስመር ላይ ለውጦችን ሊያደርጉ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል።
የጣና ሞገዶች በነገው ጨዋታ በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በአንፃሩ የመስመር ተጫዋቹ ግርማ ዲሳሳ በገዳት መልስ ቡድኑን ለማገልገል ዝግጁ ሆኗል።
የመጀመርያው የሊግ ጨዋታቸው ነብሮቹን በማሸነፍ የጀመሩት ቻምፒዮኖቹ በዚ ጨዋታ አሁንም በርካታ ተጫዋቾቻቸው በጉዳት ቢያጡም ሁለት ውሳኝ ተጫዋቾቻቸው ከቅጣት መልስ ማግኘታቸው ቀላል ግምት አይሰጣቸውም። በቅድመ ውድድር ቆይታቸው እና በመጀመርያው የሊግ ጨዋታቸው 4-2-3-1 እና 4-4-2 አቀያይረው የተጫወቱት መቐለዎች ከወዲሁ በነገው ጨዋታ የሚከተሉት አደራደር ለመገመት አዳጋች ቢሆንም ተጋጣሚያቸው ባህር ዳር ከተማ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እንደታየው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚጥር ቡድን እንደመሆኑ በአማካይ ቦታ ላይ በርካታ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዚ ጨዋታ ሁለት አጥቂ ያጣምራሉ ተብለው የማይጠበቁት መቐለዎች ኦኪኪ ኦፎላቢን ከቅጣት መልስ ማግኘታቸውን ተከትሎ አማኑኤል ገብረሚካኤል ወደ መስመር ይመልሳሉ ተብሎ ይገመታል።
በተለይም በተጫዋቾች ጉዳት ምክንያት የፈጠራ አቅምን ያጣው የአማካይ ክፍላቸው የቅርፅ ለውጥ እንደሚያደርጉ ሲጠበቅ የመስመር አጨዋወታቸው ሁነኛ የማጥቁያ መንገድ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
መቐለዎች በነገው ጨዋታ አምበሉ ሚካኤል ደስታ፣ ዮናስ ገረመው፣ ያሬድ ብርሃኑ እና አሌክስ ተሰማን በጉዳት ሲያጡ ቢያድግልኝ ኤልያስን ከጉዳት ኦኪኪ ኦፎላቢ እና ሥዩም ተስፋዬን ከቅጣት መልስ ቡድናቸው የሚያገለግሉ ተጫዋቾች ናቸው።
እርስ በርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ሁለት ጊዜ (2011) ተገናኝተው ሁለቱም በየሜዳቸው ያደረጓቸውን ጨዋታዎች 1-0 በሆነ ተመሳሳይ ውጤት አሸንፈዋል።
ቀጥታ ስርጭት
ጨዋታው በአማራ ቴሌቪዥን እንደሚተላለፍ ተቋሙ አስታውቋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ባህርዳር ከተማ (4-3-3)
ሀሪሰን ሄሱ
ሳላምላክ ተገኝ – አዳማ ሲሶኮ – አቤል ውዱ – ሳሙኤል ተስፋዬ
ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ዳንኤል ኃይሉ – ፍፁም ዓለሙ
ዜናው ፈረደ – ማማዱ ሲዲቤ – ወሰኑ ዓሊ
መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)
ፊሊፕ ኦቮኖ
ሥዩም ተስፋዬ – ላውረንስ ኤድዋርድ – አሚን ነስሩ – አስናቀ ሞገስ
ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ዳንኤል ደምሴ
ኤፍሬም አሻሞ – ያሬድ ከበደ – አማኑኤል ገብረሚካኤል
ኦኪኪ ኦፎላቢ
© ሶከር ኢትዮጵያ