ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ፋሲል ከነማ ከ ድሬዳዋ ከተማ ነገ በ9:00 ፋሲለደስ ስታዲየም ላይ የሚያደርጉትን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ከዐምናው የፕሪምየር ሊግ ፍፃሜ በኋላ የጥሎ ማለፍ፣ የቅድመ ውድድር ጨዋታዎች፣ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታዎችን ከመቀመጫ ከተማው ርቆ ያከናወነው ፋሲል ከነማ ከወራት በኋላ በሜዳው ጨዋታ ያደርጋል።

ፋሲል በመጀመርያ ጨዋታው ያለ ጎል አቻ እንደመለያየቱ አጀማመሩን ለማሳመር ከዚህኛው ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ የማግኘት ግዴታ ውስጥ ሆኖ ጨዋታውን ያደርጋል። በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተው የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ቡድን በነገውም ጨዋታ ተመሳሳዩን አጨዋወት ይዞ በመግባት አፈግፍጎ መጫወትን ምርጫው በሚያደርገው ተጋጣሚው ድሬዳዋ የመከላከል ወረዳ ቀዳዳዎችን ለማስከፈት ጥረት እንደሚያደርግ ይገመታል። በሦስት አማካዮች የሚዋቀረው ቡድኑ በመሐለኛው የሜዳ ክፍል የተሳኩ ቅብብሎች በማድረግ የጎል ዕድሎችን ለመፍጠርም በአራት አማካዮች ከተዋቀረው የድሬዳዋ አማካይ ክፍል ጋር ከፍተኛ ትግል ይጠብቀዋል።

በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ ላይ የተጎዳው እንየው ካሣሁን ከጉዳቱ ያላገገመ ሲሆን በጉዳት ላይ የቆዩት አብዱራህማን ሙባረክ፣ ሰለሞን ሀብቴ፣ ኤፍሬም ክፍሌ፣ መልካሙ ታውፈር እና ጀማል ጣሰው አሁንም በጉዳት ለቡድኑ ግልጋሎት አይሰጡም። በአንፃሩ ቡድኑ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች የለም።

የመጀመርያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ ተሸንፎ የጀመረው ድሬዳዋ ከተማ በድጋሚ ከሜዳው ውጪ ጨዋታ ያደርጋል። ይህም ቡድኑ ቢያንስ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ለማግኘት ያለመ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በበርካታ የአማካይ ተጫዋቾችን የተዋቀረው ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር በተደረገው ጨዋታ እንደተስተዋለው አመዛኞቹን ተጫዋቾች ከኳስ ጀርባ አድርጎ የፋሲልን በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ የማጥቃት እንቅስቃሴ በመግታት በሚገኙ ክፍተቶች በመልሶ ማጥቃት እንደሚንቀሳቀስ ይገመታል። ከብቸኛው የፊት አጥቂ ሪችሞንድ አዶንጎ ጀርባ እንደሚሰለፍ የሚጠበቀው ኤልያስ ማሞ ከአራቱ አማካዮች እና ከአጥቂው ጋር የሚፈጥረው ግንኙነትም በርካታ ጎል እድል ለመፍጠር ለሚቸገረው ድሬዳዋ ከተማ ውጤታማነት ወሳኝ ነው።

ድሬዳዋ ከተማ በጨዋታው የወሳኝ ተጫዋቾቹ ሳምሶን አሰፋ እና ረመዳን ናስር ግልጋሎት አሁንም አያገኝም። በተጨማሪም በሀዋሳው ጨዋታ የተጎዳው የመስመር አማካዩ ያሬድ ታደሰ እና የቀይ ካርድ የተመለከተው ዘሪሁን አንሼቦ በቅጣት የማይሰለፉ ይሆናል።

ድሬዳዋ ከተማ ከተጫዋቾቹ በተጨማሪ የአሰልጣኝ ስምዖን ዓባይን ግልጋሎት በጨዋታው አያገኝም። አሰልጣኙ ከባለፈው ዓመት በዞረ ቅጣት የመጀመርያው ጨዋታም ያለፋቸው ሲሆን በዚህ ጨዋታ ቅጣታቸውን ይጨርሳሉ። ምክትሉ ፍስሀ ጥዑመልሳንም ቡድኑን የሚመሩ ይሆናል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– በሊጉ እስካሁን ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል። ፋሲል ከነማ ኹለት ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ሲሆን አንድ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ አሸንፏል። በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

– በተገናኙባቸው 6 የሊግ ጨዋታዎች ስድስት ጎሎች ብቻ የተቆጠሩ ሲሆን ፋሲል ከነማ አራት፤ ድሬዳዋ ከተማ ኹለት ጎሎች አስቆጥረዋል።

– ጎንደር ላይ በተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ ኹለቱን ሲያሸንፍ አንዱን አቻ ተለያይተዋል።

– ዐምና ያደረጓቸው ኹለቱንም ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ (0-1 እና 2-0) አሸንፏል።

– ድሬዳዋ ከተማ ወደ ጎንደር ተጉዞ ድል አስመዝግቦም ሆነ ጎል አስቆጥሮ አያውቅም።

– ለመጨረሻ ጊዜ ሁለቱ ቡድኖች የተጫወቱት በአዳማ ከተማ ዋንጫ ሲሆን ፋሲል ከነማ በኦሴይ ማዊሊ እና ሙጂብ ቃሲም ጎሎች 2-0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሳማኬ ሚኬል

ሰዒድ ሀሰን – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ጋብሬል አህመድ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው

ሽመክት ጉግሳ – ሙጂብ ቃሲም – ኦሰይ ማውሊ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-1-1)

ፍሬው ጌታሁን

ፍሬዘር ካሣ – በረከት ሳሙኤል – ያሬድ ዘውድነህ – አማረ በቀለ

ዋለልኝ ገብሬ – አማኑኤል ተሾመ – ፍሬድ ሙሸንዲ – ያሬድ ሀሰን

ኤልያስ ማሞ

ሪችሞንድ ኦዶንጎ


© ሶከር ኢትዮጵያ