የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ነገ ይጀመራል

አስራ አንድ ክለቦችን የሚያሳትፈው የ2012 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረግ አንድ መርሐ ግብር ጅማሮውን ያደርጋል፡፡

ነገ በብቸኝነት የሚደረገው ዲላ ላይ በ9:00 ጌዴኦ ዲላ ከ አርባምንጭ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው።

የስድስት ወራት ደመወዝ ክፍያን ለቀድሞ አሰልጣኙ እየሩሳሌም ነጋሽ ባለመክፈሉ ምክንያት አዲስ ያስፈረማቸውን ተጫዋቾችን በፌድሬሽኑ ማፀደቅ ያልቻለው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በመርሐ-ግብሩ መሠረት ድሬዳዋ ከተማን በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚገጥም የሚጠበቅ ቢሆንም ለአሰልጣኟ ክፍያን መፈፀም ካልቻለ በውድድሩ እንደማይሳተፍ ፌዴሬሽኑ ለክለቡ ማሳወቁን ሰምተናል፡፡

መቐለ 70 እንደርታን አራፊ ቡድን የሚያደርገው ይህ ሳምንት በማድረግ ዕሁድ በ9:00 ሲቀጥል የዐምናው ቻምፒዮን አዳማ ከተማን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ላይ የሚያገናኘው ጨዋታ የዚህ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ነው።

የጥሎ ማለፉ ቻምፒዮን ሀዋሳ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም የፊታችን ማክሰኞ አቃቂ ቃሊቲን ይገጥማል፡፡ ረቡዕ ደግሞ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የይራዘምልኝ ደብዳቤ አስገብቶ ተቀባይነት ያላገኘው እና ከመፍረስ ተርፎ በቅርቡ ዝግጅቱን የጀመረው አዲስ አበባ ከተማ መከላከያን ይገጥማል።

የዘንድሮው ውድድር በ14 ክለቦች መካአል ለማካሄድ ታስቦ ነበረ ቢሆንም ዐምና በውድድሩ ላይ ሲሳተፍ የነበረው ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ በሁለተኛው ውድድር ለመሳተፍ በመወሰኑ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዝዮን በማምራቱ እንዲሁም ጥረት ኮርፖሬት በመፍረሱ በ11 ክለቦች መካከል የሚካሄድ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ