ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

በአዳማ አበበ ቢቂላ የሚከናከነው የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ እንደሚከተለው ተዳሷል።

በመጀመርያ ሳምንት ጨዋታቸው ከፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ጎል ነጥብ የነጋሩት ሁለቱ ቡድኖች ነገ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ጎል እና የሦስት ነጥብ ለማስመዝገብ ይፎካከራሉ።

አዳማ ከተማ በርከት ያሉ የማጥቃት ተጫዋቾችን በስብስቡ እንደመያዙ አማራጩ ሰፊ የሆነ ቡድን ነው። ሆኖም ቡድኑ እንደሚፈጥረው በርካታ የጎል ዕድል በፊት መስመር ላይ ሥል አለመሆኑ ጎሎችን እንዳያስቆጥር እያደረገው ይገኛል። ባለፈው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በተደጋጋሚ ወደ ጎል የደረሱት አዳማዎች በነገው ጨዋታም ከፋሲል ጋር ተቀራራቢ አጨዋወት ያላቸው ወልቂጤ ከተማዎች በማጥቃት ወቅት ከጀርባቸው የሚፈጥሩትን ክፍተት በመጠቀም በፈጣን አጥቂዎቻቸው የጎል ዕድሎችን እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል። ቡልቻ ሹራ እና ዳዋ ሆቴሳ ዕድሎችን ወደ ጎል የመቀየር አቅማቸውን ማሳደግ ከቻሉም የዓመቱ የመጀመርያ ሦስት ነጥባቸውን ለማግኘት እንደማይቸገሩ ይገመታል።

አዳማ ከተማ ከነዓን ማርክነህን በጉዳት ለጨዋታው የመጠቀሙ ጉዳይ አጠራጣሪ ከመሆኑ በቀር በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች አይኖርም።

ወልቂጤዎች በታሪክ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታቸውን ከሪከርድ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ጎል አቻ በመለያየት የጀመሩ ሲሆን በሜዳው ጠንካራ ከሆነው አዳማ ከተማ ጠንካራ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የተመለከትነው ወልቂጤ ከተማ በኳስ ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ቡድን ቢሆንም ገዘፍ ያለ ተክለ ሰውነት ያላቸው አጥቂዎችን የሚጠቀም እንደመሆኑ ቀጥተኛ አጨዋወትን እንደ አማራጭነት የሚጠቀም ቡድን እንደሚሆን በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ፍንጭ ሰጥቷል። በዚህም በነገው ጨዋታ ባለሜዳው ቡድን በማጥቃት ወቅት የሚፈጥረውን ክፍተት ለመጠቀም ጃኮ አራፋት እና አህመድ ሁሴንን ማዕከል ያደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች ይጠበቃሉ። በጊዮርጊሱ ጨዋታ ከቡድኑ ተነጥለው የታዩት ሁለቱ አጥቂዎች እርስ በእርስም ሆነ ከአማካዮች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነትም ከሊጉ ጠጣር የተከላካይ ክፍሎች አንዱ የሆነው አዳማ ከተማ ላይ ነጥብ ይዞ ለመመለስ ቁልፍ ይሆናል።

ወልቂጤ ባለፈው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን ከገጠመው ስብስቡ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ይበልጣል ሽባባውን በጉዳት ሲያጣ በጉዳት ርቀው የቆየው ፍፁም ተፈሪም ይህ ጨዋታ ያመልጠዋል። ከጉዳታቸው እያገገሙ የሚገኙት መሐመድ ሻፊ እና ጫላ ተሺታም በዚህ ጨዋታ ላይ አይሰለፉም።

የእርስ በርስ ግንኙነት

ወልቂጤ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ያደገው ዘንድሮ እንደመሆኑ የሁለቱ ግንኙነት በሊጉ የመጀመርያ ይሆናል።

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ጃኮ ፔንዜ

ሱሌይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – መናፍ ዐወል – ቴዎድሮስ በቀለ

አዲስ ህንፃ – አማኑኤል ጎበና

ፉአድ ፈረጃ – በረከት ደስታ – ዳዋ ሆቴሳ

ቡልቻ ሹራ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3 / 4-1-3-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ይበልጣል ሽባባው – ቶማስ ስምረቱ – ዳግም ንጉሴ – አቤኔዜር ኦቴ

ሄኖክ አወቀ – አልሳሪ አልመሐዲ – አዳነ ግርማ – ዓባይነህ ፌኖ

አህመድ ሁሴን – ጃኮ አራፋት


© ሶከር ኢትዮጵያ