ሪፖርት | አዳማ ከተማ በሜዳው ድል ቀንቶታል

የሊጉን ተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታ በሜዳው አበበ ቢቂላ ስታድየም ያደረገው አዳማ ከተማ ወልቂጤ ከተማን አስተናግዶ በዳዋ ሆቴሳ ብቸኛ ጎል በማሸነፍ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያውን ሦስት ነጥቡን አሳክቷል።

አዳማ በመጀመርያ ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር ያለ ጎል በአቻ ውጤት ከተጠናቀው ቡድኑ በጉዳት ላይ የሚገኘው ከነዓን ማርክነህን በሚካኤል ጆርጅ በመተካት ወደ ሜዳ ሲገባ፤ አዲስ አዳጊው ወልቂጤ ከተማ በባቱ ከተማ ሼር ሜዳ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ጎል በአቻ ውጤት ከተለያየው ስብስብ ይበልጣል ሽባባው እና አምበሉ አዳነ ግርማን በማሳረፍ በምትካቸው በረከት ጥጋቡ እና ዐወል መሐመድን በመያዝ ወደ ሜዳ ገብቷል።

ብዙም ሳቢ ያልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ባልተደራጀ እንቅስቃሴ በርከት ያሉ የጎል እድሎችን ሳያስመለክተን ተጠናቋል። ሆኖም በጨዋታው ጅማሬ ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ በ2ኛው ደቂቃ ወልቂጤዎች ሳይጠበቅ ወደ ፊት በቀኝ መስመር በኩል ሄደው አህመድ ሁሴን ወደ ጎል ያሻገረውን ጃኮ አራፋት ሲመታው በተከላካዮች ተሸራርፎ የቀረውን አምስት ከሀምሳ ፊት ለፊት ነፃ የጎል አጋጣሚ ዓባይነህ ፌኖ አግኝቶ ጎል አስቆጠረ ሲባል በቀላሉ ለአዳማው ግብጠባቂ ጃኮ ፔንዜ ያሳቀፈው ኳስ ምን አልባት የጨዋታውን አጠቃላይ ሂደት የሚቀይር ለወልቂጤዎች መልካም አጋጣሚ ነበር።

ከዚህ በኃላ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ ይልቁኑም በማጥቃት ሽግግሩ ላይ ሁለቱም ቡድኖች ይከተሉት የነበረው አጨዋወት ዝብርቅርቅ ያለ መሆኑ በተፈለገው ደረጃ ተመልካችን የማይስብ እና ወደማሰልቸት ያመራ ጨዋታ ሆኖ አልፏል።

ያም ቢሆን አዲስ ፈራሚው የአዳማው አማካይ አማኑኤል ጎበና በግራ መስመር ከበረከት ደስታ ጋር ይዘውት የሄዱትን ኳስ በረከት ደስታ ተከላካዮችን በማለፍ በጥሩ ሁኔታ አመቻችቶ ያቀበለውን በሰውነቱ ተከላካዮችን በመሸፈን በግራ እግሩ ለአዳማ የጨዋታውን ብቸኛ ጎል በ14ኛው ደቂቃ ደዋ ሆቴሳ አስቆጥሯል። ጎሉም ለአዳማም፣ ለዳዋ ሆቴሳም የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጎል ሆና ተመዝግባለች። በጎሉ መቆጠር የጨዋታው መንፈስ ይቀየራል ቢባልም ብዙም የተለየ ነገር ሳይኖር ቀጥሏል።

ወልቂጤዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም የማጥቃት ሽግግራቸው አዝጋሚ በመሆኑ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተቸግረዋል። ወደ እረፍት መዳረሻ የመጨረሻዎቹ ሰባት ደቂቃዎች ላይ ተጭነው ጎል ፍለጋ በተደጋጋሚ ወደ አዳማ ግብ ክልል የደረሱ ሲሆን 41ኛው ደቂቃ ሄኖክ አወቀ በግራ መስመር በረከት ደስታን በጥሩ ሁኔታ በማለፍ በግራ እግሩ ወደ ጎል አክርሮ የመታውን ግብጠባቂው ጃኮ ፔንዜ ቢተፋውም በድጋሚ ኳሱን በጥንቃቄ ይዟታል።

ከእረፍት መልስ ብዙም ሳይሻሻል የቀጠለው ጨዋታ እምብዛም ወደ ጎል በመድረሰ የሚደረግ ሙከራም ሆነ የተደራጀ የማይቆራረጥ እንቅስቃሴ ሳያስመልክተን 60ኛው ደቂቃ ደርሶ ከመሐል ሜዳ ከሚካኤል ጆርጅ የሾለከለትን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ ከውሳኔ ችግር ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ የተሻለ ወደ ጎል የቀረበ ሙከራ ነበር።

ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅ ትኩረት ሳቢ የነበረው በዳዋ ሆቴሳ እና በበቃሉ ገነነ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት አንገት ለአንገት ተያይዘው የፈጠሩትን ግርግር የጨዋታው ዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ ማስጠንቀቂያ ካርድ እንኳ ሳይሰጡ በዝምታ ማለፋቸው አስገራሚ ሆኖ አልፏል።

የተጨዋች ቅያሪ አስቀድመው የጨረሱት ወልቂጤዎች 81ኛው ደቂቃ ተከላካያቸው ቶማስ ስምረቱ ጉዳት አስተናግዶ ህክምናውን እስኪከታተል ድረስ ለተወሰኑ ደቂቃዎች በጎዶሎ ልጅ ለመጫወት ተገደው እንደነበረ አይተናል።

በመጨረሻም ወልቂጤዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ በተደጋጋሚ ከቆሙ ኳሶች የአዳማን የግብ ክልል ለመፈተሽ ጥረት ቢያደርጉም ጠንካራውን የአዳማ የመከላከል ወረዳን ሰብረው ለመግባት ተቸግረው ጨዋታው በአዳማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሦስት ነጥብ ሲያሳካ አዲስ አዳጊው ወልቂጤ ከተማ በታሪኩ የመጀመርያ የሊጉን ሽንፈት አስተናግዷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ