ጎንደር ላይ በተደረገው የሊጉ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ፋሲል ከነማ ከሙጂብ ቃሲም እና ሽመክት ጉግሳ ድንቅ ብቃት ጋር ድሬዳዋ ከተማን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል። ሙጂብ ቃሲምም የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ባለ ሐት-ትሪክ ሆኗል።
ከረጅም ወራት በኋላ ወደ ጎንደር የተመለሱት ዐፄዎቹ ከጨዋታው በፊት ከሊጉ መጀመር አስቀድሞ ያሳኩትን የአሸናፊዎች አሸናፊ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ለደጋፊዎቻቸው ሜዳ ላይ አሳይተዋል።
በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ከአዳማ ከተማ ጋር 0 – 0 ከተለያየው ስብስብ ኦሲ ማውሊን በኢዙ አዙካ በመተካት ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። በእንግዶቹ በኩል ደግሞ ከሳምንቱ ጨዋታ ቅጣት ላይ የሚገኘው ዘሪሁን አንሼቦ በያሬድ ዘውድነህ የተተካበት ቅያሪ ተስተውሏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያሉ ሙከራዎች ባደረጉት ዐፄዎቹ በኩል ጨዋታው እንደተጀመረ በግራ መስመር አምሳሉ ጥላሁን ያሻማውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በጭንቅላት በመግጨት ወደ ግብ የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ተጠግቶ የወጣበት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር። ወደፊት ተጭነው በመጫወት ጥረታቸውን የቀጠሉት ዐፄዎቹ 8ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ተገጭቶ የተመለሰ ኳስ ሙጂብ ቃሲም በመልሶ ማጥቃት ተከላካዮችን አልፎ በቀጥታ ወደግብ አክርሮ በመምታት ባስቆጠረው ግብ መሪ መሆን ችለዋል።
ፋሲሎች ከግቡ መቆጠር በኋላም ብልጫ ቢወስዱም በርካታ ዕድሎችን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ከዚህ ውስጥ በግራ መስመር አምሳሉ ጥላሁን፣ ሽመክት ጉግሳ እንዲሁም ሙጂብ ቃሲም በፈጠሩት ጥምረት 16ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ያሻገረለትን ኳስ ሙጅብ ግብ ጠባቂውን አልፎ ኳሱ ወደ ውጪ የወጣበት የሚጠቀስ ነበር። እንዲሁም ወደ ኋላ እየተመለሰ ኳሶችን በመደረጀት እና በመቀበል ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ሙጂብ 21ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ያገኘውን ለሱራፌል ዳኛቸው አሻግሮለት ሱራፌል ወደ ግብ አክርሮ የመታው እና ግብ ጠባቂው ያዳነበት፤ ቀጥሎም ሽመክት ጉግሳ ወደ ግብ አክርሮ መትቶት በተከላካዮች ተገጭቶ የተመለሰው ኳስም ለግብ የቀረበ ነበር። በተቀራራቢ ደቂቃ በተፈጠረ ሌላ አጋጣሚም ሰራፌል ዳኛቸው ከሰዒድ ሀሰን የተሻገረለትን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ የግቡን የቀኝ ቋሚ ተጠግቶ ወጥቶበታል።
በእንግዳዎቹ በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የመከላከል ሂደት ቢኖርም የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ክፍተት ነበረባቸው። ድሬዎች በተደጋጋሚ የቆሙ ኳሶችን ከቅጣት ምት ማግኘት የቻሉ ቢሆንም ያገኙትን አጋጣሚ መጠቀም አልቻሉም። በሙከራ ደረጃ ግን 24ኛው ደቂቃ ላይ ሙኸዲን ሙሳ ከሳጥን ውጪ ወደግብ አክርሮ የመታው ኳስ የሚጠበቅ ነበር። በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማግኘት ሲሞክሩ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ 39ኛው ደቂቃ ላይ ኦዶንጎ ሬችሞንድ ከሳጥን ውጪ ወደግብ አክርሮ የመታው እና ግብ ጠባቂው ያዳነበትም በመጀመሪያው አጋማሽ ከሚጠቀሱ ሙከራዎቻቸው ውስጥ የሚካተት ነው።
በሁለተኛው አጋማሽ ለውጦችን አድርገው የገቡት ባለሜዳዎቹ የተሻለ የመሀል ሜዳ ብልጫ እንዲሁም በመጀመሪያው አጋማሸ ከነበረባቸው ክፍተት ራሳቸውን አስተካለው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። 61ኛው ደቂቃ ላይም በቀኝ በኩል ማዊሊ ከሱራፌል የተቀበለውን ኳስ ከቀኝ ሳጥን ጠርዝ ለሽመክት አሻግሮለት ሽመክት ወደ ግብ አክርሮ በመምታት ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ወደ ቀኝ መስመር ባመዘነው የቡድኑ የማጥቃት ሂደት ሽመክት ከሰዒድ የተሻገረለትን ኳስ በተመሳሳይ ባታ ላይ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ አክርሮ በመምታት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ግብም አክሏል። በመቀጠል ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ሽመክት ጉግሳ 80ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ ለሙጅብ አሻግሮለት ሙጅብ ወደግብ በመቀየር የግብ ልዩነቱን ማስፋት ችሏል።
ፋሲሎች የመሀል ክፍሉን በሦስት የተከላካይ አማካዮች በማደራጀት ኳስ ከወገብ በታች እንዳያልፍ ዘግተው በመጫወት በፈጣን እና ንክኪ በበዛበት ጨዋታ ቶሎ ቶሎ ወደ ድሬድዋ ግብ ክልል ውስጥ መድረሳቸውን ቀጥለዋል። በዚህም 84ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ሱራፌል መሀል ላይ ሦስት ተጫዋቾች አልፎ አሻግሮለት ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ተጠግቶ ወጥቶበት ሐት-ትሪክ መስራት የሚችልበትን አጋጣሚ አሳልፎበታል።
በጨዋታው ሁለት ግቦች ላይ ተሳትፎ ያደረገው ሰዒድ ሀሰን በቀኝ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ በተመሳሳይ ሁኔታ ለሙጅብ ቃሲም አሻግሮለት ሙጅብ ቃሲም ለዐፄዎቹ አምስተኛ ለራሱ ደግሞ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ጎል አስቆጥሯል።
ድሬዳዋ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ የበላይነት ተወስዶባቸው ከመጀመሪያው አጋማሽ በባሰ መልኩ ተዳክመው ታይተዋል። በሙከራ ደረጃም 72ኛ ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞ ወደ ግብ አክርሮ መቶት የግቡ ቋሚን ተጠግቶ የወጣው ኳስ ነበር ሊጠቀስ የሚችለው። በዚህም ልዩነቱን ማጥበብ ሳይችሉ 5-0 ለመሸነፍ ተገደዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ