የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 1-1 ሀዋሳ ከተማ

በ2ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ላይ ሀዲያ ሆሳዕና ከሀዋሳ ከተማ ተገናኝተው 1-1 በሆነ ውጤት ከተለያዩ በኃላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንዲህ ሰጥተውናል፡፡

“ነጥብ መጋራታችን አይገባንም ” ግርማ ታደሰ – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለ ጨዋታው

“እንደተጋጣሚያችን እንቅስቃሴ ምናልባት ይዘው የመጡት የአጨዋወት መንገድ ሜዳ አጥብቦ መጫወት ነበር። ያ ለኛ ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። ብልጫ መውሰድ ብንችልም አቻ ውጤት አይገባንም። ያገኘናቸውን የግብ አጋጣሚዎች የመጠቀም አቅማችን አነስተኛ በመሆኑ እንጂ ነጥብ መጋራታችን አይገባንም። ሀዋሳ በመልሶ ማጥቃት ነበር አብዛኛውን ኳስ ሲጫወት የነበረው። እና ያ ደግሞ ይዘን የገባነውን ዕቅድ በአግባቡ እንዳንተገብር በተወሰነ መልኩ ጫና ፈጥሮብናል፡፡ ውጤቱ በቂ ነው ብዬ አላስብም። ተጋጣሚያችን አብዛኛውን በሜዳው ላይ ነበር የሚያሳልፈው። ሰዓት የማባከን የጨዋታውን ግለት የማቀዝቀዝ ሲስተሞችን ነበር ይዘው የገቡት። ይህ ደግሞ ለኛ ምቹ ሁኔታ አልፈጠረልንም።”

ስለአጨራረስ ችግር

“በማጥቃቱም ሆነ የመከላከሉ በጣም የተሻለ ነገር አለን። አጨራረሳችን ላይ ግን በደንብ መስራት ይጠበቅብናል። ተመሳሳይ ችግሮችን እያየን ነው፤ ባለፈው በመቐለም ጨዋታ ዛሬም ያየነው ያንን ነው። ምናልባት በቂ ልጆች አሉን ማጥቃቱ እና እንዴት እናስቆጥራለን በሚሉት ላይ በደንብ እንሰራለን። ሁሌም ግን አጥቅተን የመጫወት አቅማችንን ነው የምናስቀጥለው። የመከላከል ሚና ይዘን አንገባም። አብዛኛውን ሰዓት በማጥቃት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ነው የምናደርገው ፤ ያ ደግሞ ያዋጣናል ብዬ አስባለው። አጨራረስ ላይ በተወሰነ መልኩ ክፍተት አለ ያን እናስተካክላለን በእርግጠኝነት”

“ስለተከላከልን ነው አንድ ነጥብ ይዘን የወጣነው” አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደሚከብደን ተነጋግረናል፤ አውቀነዋል። ምክንያቱም አንደኛ ሆሳዕና የመጀመሪያው ነው በፕሪምየር ሊጉ በሜዳው ሲጫወት። ሁለተኛ ደግሞ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ተሸንፏል። አዳማ ላይ ለዋንጫ በሲቲ ካፕ ተገናኝተን ዋንጫን ወስደንበታል። ከዚያም ፕሪምየር ሊጉ ሲጀምር ደግሞ መቐለ ላይ ተሸንፎ ነው የመጣው። ስለዚህ በጣም ከባድ እንደሚሆን ጠብቀን ነበር። የጠበቅነውን ሲያደርጉ ነው የነበሩት። በተለይ የመጀመሪያው አጋማሽ ሀያ እና ሀያ አምስት ደቂቃዎች በጣም ከባድ ጨዋታ ነበር፡፡ ያን ሰዓት ጎል ያለማግባታቸው ለኛ ጥሩ ነገር ፈጥሮልናል፡፡ ልጆቻችንም በሂደት ጥሩ መሆን ችለዋል፡፡”

ስለቡድኑ የመከላከል አቀራረብ

“ስለተከላከልን ነው አንድ ነጥብ ይዘን የወጣነው። ያን ማድረግ ባንችል ኖሮ ብዙ ነገሮች ለኛ ምቹ አልነበሩም። አንደኛ ስንሰራ የከረምንበት ሜዳ ከዚህ ሜዳ ጋር በፍፁም አይገናኝም። ኳስ ይዘን እንጫወት ብንልም የማይሆን ነገር ነው፡፡ ሁለተኛ እነሱ ኃይል ቀላቅለው ማሸነፍን ከመጀመሪያው አስበው ነበር የገቡት። ኃላችንን ባንዘጋው ኖሮ ክፍተቶች ይፈጠሩ ነበር። ፊት ለፊት ያሉ አጥቂዎች የውጪ ተጫዋቾች ናቸው። ትንሽ ክፍተት ሰጥተናቸው ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ይሄ አይሆንም ነበር። አስበንበት የመጣነው ነው፡፡ ያደረግነው ነገር በጣም ትክክል ነው፡፡”

ስለ ፍፁም ቅጣት ምቱ

“ይሄ ከባድ ነው ፤ የዳኝነት ሙያ ላይ መግባት አስፈላጊ አይደለም። ግን አንዳንዳንድ ጊዜ ህጉ እጅ ወደ ኳስ ኳስ ወደ እጅ የሚለው ነገር አለ። በቆመበት ነው ኳሱ የመታው ፤ ለዛ ደግሞ በጣም የሚቀርበው የመስመር ዳኛው ነው፡፡ መስመር ዳኛ ምንም የውሳኔ እንቅስቃሴን አላሳየም። በዛ ሁኔታ ላይ ጎሉን እንዳገባን ነው ይሄ ሁኔታ የተፈጠረው። ቢሆንም ግን ዳኝነቱ ጥሩ ነው፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ