ቻን 2016፡ ኮትዲቯርን ያሸነፈችው ማሊ ከዲ.ሪ. ኮንጎ ጋር ለዋንጫ ትፋለማለች 

 

በአፍሪካ ሃገራት ዋንጫ (ቻን) ፍፃሜ ማሊ ከዲ.ሪ. ኮንጎ ይገናኛሉ፡፡ በሩዋንዳ አዘጋጅነት እየተደረገ ባለው በየሃገራቸው ሊጎች ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የተፈቀደው ውድድር ዛሬ ማሊ ኮትዲቯርን 1-0 በማሸነፍ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኗን አረጋግጣለች፡፡

የጨዋታ የበላይነት የነበራት ማሊ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ተቀይሮ የገባው የቪስ ቢሶማ ባስቆጠራት ግብ ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ አልፈዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የዝሆኖቹ ግብ ጠባቂ ባድራ አሊ ሳንጋሬ የማማዱ ኩሊባሌን ፍፁም ቅጣት ምት አድኗል፡፡ የክለብ እግር ኳሱን ለኤኤስ ሪያል የሚጫወተው ቢሶማ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡

የማሊው አሰልጣኝ ጂብሪል ድራሜ ከጠንካራዎቹ የማሊ ክለቦች ስታደ ማሊያን፣ ጆሊባ፣ ኢለቨን ክሬተርስ እና ከኤኤስ ሪያል ተጫዋቾችን በስብስባቸው ያካተቱ ሲሆን ሴኔጋል ባዘጋጀቸው የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ የተሳተፉ ተጫዋቾችንንም ጨምረው ይዘዋል፡፡

የማሊ እና ኮትዲቯር ጨዋታ በአራተኛ ዳኝነት የመራው ኢትዮጵያዊው ባምላክ ተሰማ ነው፡፡ ባምላክ ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን እና አንድ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ በመሃል ዳኝነት ሲመራ የዛሬውን ጨዋታ ጨምሮ ሁለት ግዜያት አራተኛ ዳኛ ነበር፡፡

በቻን 2016 ፍፃሜ ኮንጎ ከማሊ ትጫወታለች፡፡ ማሊ ጨዋታውን ማሸነፍ ከቻለች አራተኛው የውድድሩ አሸናፊ ስትሆን የመጀመሪያዋ የምዕራብ አፍሪካ ሃገርም ትሆናለች፡፡ ኮንጎ ጨዋታውን ካሸነፈች ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ የቻን ዋንጫን ታነሳለች፡፡

የውድድሩን ኮከብ ግብ አግቢነት በቅርቡ ለዋይዳድ ካዛብላንካ የፈረመው የናይጄሪያው ኤልቪስ ቺካታራ እና የካርቴጅ ንስሮቹ (ቱኒዚያ) አጥቂ አህመድ አካቺ በ4 ግብ ይመራሉ፡፡

ያጋሩ