የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተሻሻለውን ሎጎ አፀደቀ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ከዚህ ቀደም ሲጠቀምበት የነበረውን መለያ (ሎጎ) በማሻሻል በዛሬው ጠቅላላ ጉባዔ አፀድቋል።

በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም ከነበረው ሎጎ ላይ ከእግርኳሱ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና የሌላቸው የነበሩት የእህል ምርት እንዲሁም የአንድ ትጥቅ አምራች የመጫወቻ ጫማ የነበረው ሲሆን አዲስ በተሻሻለው ሎጎ ሁለቱ እንዲወጡ ተደርገዋል።

በተጨማሪም በሎጎው ጠርዝ ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና የፌደሬሽኑ ስያሜ በአማርኛና እንግሊዝኛ ፅሁፍ እኩል 50% በጠርዙ ላይ ድርሻ የነበራቸው ሲሆኑ በተሻሻለው ላይ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ የተሻለ ድርሻ እንዲኖረው ተደርጓል።

በመቀጠልም በተሰብሳቢዎች የተወሰኑ ሀሳቦች የተሰጡ ሲሆን በተለይም ከኳሱ ምስል ጋር የሀገሪቱ ካርታ ቢካተት እንዲሁም ኳሱ በምስል ከሚሆን በተሻለ መልኩ ገለጭ በሆነ መልኩ ቢቀርብ የሚል ሀሳብ ከአባላት ቢቀርብም ሀገሪቷን የሚገልፅ ሰንደቅ ዓላማ መኖሩ በቂ ነው በሚል ምላሽ በፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ቀርቧል።

በመቀጠልም ጠቅላላ ጉባዔው በ82 ድምፅ የፌደሬሽኑን ሎጎ ለመቀየር ውሳኔ አሳልፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ