የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የከሰዓት ውሎ

ረፋድ የተጀመረው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከምሳ እረፍት በኋላ ቀጥሎ ውሏል።

የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ኤሌያስ ሽኩር ከምሳ በፊት በነበረው መርሐግብር በተነሱ ጉዳዮች ውስጥ ተቋማቸውን በቀጥታ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ምላሽ በመስጠት ተጀምሯል። በዚህም በእግርኳስ መሠረተ ልማት እንዲሁም እግርኳሱን የተዳበለው ስርዓት አልበኝነትን ለማስወገድ የተጀመሩትን ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን ይበልጥ ፍሬ እንዲያፈራ ተቀራርቦ በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ተነሳሽነት በተቋማቸው በኩል መኖሩን ገልፀዋል።
በመቀጠል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) በዘመናት ፌደሬሽኑን በአመራርነት በመሩት ግለሰቦች ውጥኖች አንዱ የሆነውን የፊፋን ኮንግረስ በመዲናችን አዲስአበባ እንዲካሄድ በማስቻላቸው ለወቅቱ የፌደሬሽኑ የበላይ አመራሮች ምስጋናቸውን አቅርበው እግርኳስና ኦሊምፒክ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው በሰው ሀይል አቅም ግንባታና በሌሎች ዘርፎች ተጋግዘው መስራት እንደሚችሉና ለዚህም ፈቃደኝነት እንዳለ ገልፀዋል።

በመቀጠልም አስቀድሞ በፀደቀው አጀንዳ መሠረት የፌደሬሽኑ የሂሳብ ሪፖርት ቀርቧል። በዚህም በፌዴሬሽኑ በ2011 የበጀት ዓመት አጠቃላይ ገቢ 201,516,090.29 ሆኖ ሲመዘገብ በአንፃሩ የፌደሬሽኑ ዓመታዊ የወጪ መጠን 117,716,378.54 በመሆን የቀረበ ሲሆን በዚህም 83,799,711.75 የሆነ ልዩነት አሳይቷል ፤ በተጨማሪም ፌደሬሽኑየሂሳብ ሪፖርቱን በመንተራስም በቲዋይ የተመሠከረለት የሂሳብ አዋቂዎች ድርጅት የበጀት ዓመቱ የኦዲት ሪፖርት ሪፖርት እንዲቀርብ ሆኗል። በኦዲት ሪፖርቱ ግኝት መሠረት ፌደሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት ሚልየን የሚጠጋ ዕዳ ያለበት ሲሆን በተጨማሪም በኦዲት ግኝቱ መሠረት በተለይ በአዲስአበባ ስታዲየም የትኬት ሽያጭን በጥቅሉ የክለቦችን ድርሻ ሳይነጠል እንደ ገቢ መመዝገቡ ፣ ባለቤት ያልተገለኘላቸው ገቢዎች ፣ አዲስ የተገዛው ህንፃ የባለቤትነት ሰርቲፊኬት አልባ መሆኑ ፣ ከ2011 በፊት የነበሩ የፌደሬሽኑ ንብረቶች በቋሚ እሴት ግመታ ላይ ምዝገባ አለመካሄድና ሌሎች ጉዳዮች በግድፈትነት ቀርበዋል።

በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ከተሰብሳቢዎች በተነሱ ጥያቄዎች ላይ የፋይናንስ ሪፖርት አቅራቢውና በኦዲተሩ ምላሽ ከተሰጠባቸው በኃላ ሁለቱ ሪፖርቶቹ በ84 ድምፅ ናአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

አስከትሎም በ2010 ግንቦት ወር ጋምቤላ ክልልን በመወከል በስራ አስፈፃሚ አባልነት ተወክለው የነበሩት አባል በግላዊ ጉዳይ ወህኒ በመውረዳቸው የተነሳ ላለፉት 6 ወራትና ከዚያ በላይ በስራአስፈፃሚ ስብሰባ ላይ መገኘት ባለመቻላቸው በምትካቸው ያለተወዳዳሪ የቀረቡትን እጩ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርነት በመስራት ላይ የሚገኙት ኦሌሬ ኦቢያው ኡጁሉ በስራ አስፈፃሚነት እንዲተኩ ተደርጓል።

ቀጥሎም በአጀንዳው መሠረት ተሻሽሎ የቀረበው የፌደሬሽኑ መለያ ሎጎ በ82 ድምፅ እንዲፀድቅ ተደርጓል።

በመቀጠልም በዋና ፀሀፊው እያሱ መርሃፅድቅ (ዶ/ር) ለዲሲፕሊን ኮሚቴ በእጩነት የቀረቡት አቶ ተፈራ ደንበል፣ አቶ ቀፀላ ደመቀና አቶ አስቻለው ከበደን የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ የቀረበ ሲሆን በቀጣይም ከጉባዔው ተሰብሳቢዎች ሀሳብ ተሰጥቶባቸዋል። በዚህም መሠረት አቶ ኢሳይያስ ለተነሱት ሀሳቦች ሲመልሱ ለዲሲፕሊን ኮሚቴ በእጩነት የቀረቡት እጩዎች በእግርኳስ ኮሚሽነርነት የሚሰሩ አለመሆናቸው ኮሚቴው ይነሳበት የነበረውን ወገንተኝነት ችግር ለማስወገድ በዋነኝነት ታሳቢ የተደረገ ሲሆን ይህን ስራ ለመከወን የግድ በእግርኳስ ኮሚሽነርነት ማገልገል ይገባቸዋል መባሉ ተገቢ አይደለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል በመጨረሻም እጬዎቹ በ79 ድምፅ በ2 ድምፀ ተአቅቦና በ1 ተቃውሞ ፀድቋል።

በተመሳሳይ ለይግባኝ ኮሚቴ በእጩነት የተቀረቡት አቶ መንግስቱ መሐሪ ለኮሚቴ ሰብሳቢነት እንዲሁም በአባልነት ደግም ሻምበል ለማ ጉተማና አቶ መሀዲ አደምኑር የስራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት የቀረበ ሲሆን ከጉዔኤው ተሰብሳቢዎች በተለይም አቶ መንግስቱ መሐሪ ከዚህ ቀደም በዲሲፕሊን ኮሚቴ ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውና በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ መድን ድርጅት ውስጥ በምክትል ስራ አስኪያጅነት ይሰሩ የነበሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ተደጋጋሚ ሀሳቦች ተነስተዋል። በተጨማሪም እጩዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተሻለ ጊዜያቸውን ሰጥተው መስራት ይኖርባቸዋል ፤ በተሰበሰው ድምፅ መሠረት የቀረቡት እጩዎች በ73 ድምፅ በ3 ተቃውሞ እንዲሁም በ8 ድምፀ ተአቅቦ ሾመታቸው ሊፀድቅ ችሏል።

ሌላኛው ጉባዔው በከሰዓት ውሎው ዋና ጉዳይ ከተሳታፊዎች ባስያዟቸው አጀንዳዎች ላይ መምከር ነበር፤ በቅድሚያም አስቀድመው ከተያዙ አጀንዳዎች መካከል በአቅራቢዎቹ ሀሳብ ለውጥ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች መሠረት የቀሩ አጀንዳዎች ስለመኖራቸውም ተገልጿል። በተለይም የሊግ ፎርማት ለውጥን በተመለከተ በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌደሬሽንና በኢትዮጵያ መድን ስፖርት ክለብ ቀርበው የነበሩት ጥያቄዎች በጊዜ ሂደት ለውጦች በመኖራቸው መቅረታቸው ተብራርቷል።

አያይዘውም የፕሪምየር ሊጉ ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በሊጉ የፎርማት ለውጥ ዙርያ ሀሳብ ሰጥተዋል። በንግግራቸው በወቅቱ የነበረው ነባራዊ ሁኔታ ጥያቄ ከመሰል ሀሳብ ከሚያራምዱ ክለቦች ጋር በጋራ በመሆን ድምፃቸውን ስለማሰማታቸው ገልፀው ፤ የዘንድሮውም ውድድር ምንም እንኳን በቀደመው አካሄድ ቢጀመርም አሁን ላይ እየታዩ ያሉት ሊበረታቱ የሚገቡ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መቀጠል የማይችሉ ከሆነ አሁንም ወደቀደመ ሀሳባቸው እንደሚመለሱ አስረግጠው ተናግረዋል።

በመቀጠል መርሐ ግብሩ ከሻይ እረፍት ሲመለስ ምንም እንኳን የጉባዔ አባላት ቁጥር እየተመናመነ የመጣ ቢሆንም ለክለቦች አስቀድሞ የ2012 የበጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከተሰብሳቢዎች ሀሳብ ተነስቶ ውይይት ተካሂዶበታል፤ በተለይም የቀድሞው የፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገ/ወልድ ገምቢ የሚባሉ ሀሳቦችን አንስተዋል። ፌደሬሽኑ በቅርቡ የተረከበውን የካፍ የልህቀት ማዕከልን በተመለከተ ፕሮጀክት ተቀርፆ ለፊፋ የገንዘብ ጥያቄ ከማቅረብ ይልቅ ለፊፋ የመጫወቻ ሜዳ እንዲሁም የቁሳቁስ ድጋፎችን መጠየቅ መንገዶችን ምች ሊያደርግ ይችላል የሚል ሀሳብ ሰጥተዋል። በተያያዘም አዲስ ለተቋቋመው የሊጉ ዓብይ ኮሚቴ አድናቆታቸውን ገልፀው በብሔራዊ ቡድንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የጥቅም ግጭት እንዳይከሰት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል። በመቀጠልም የቀረበው እቅድ በአብላጫ ድምፅ ሊፀድቅ ችሏል።

በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ በማጠቃለያ ንግግር በዚህ መልኩ አድርገዋል

“እግርኳሳችን እንዲለወጥ ከተፈለገ እዚህ ቤት የተሰበሰብነው አካላት የየድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል ፤ እግርኳሱን በየስፍራው ተደራሽ ማድረግ ከቻልን እግርኳሳችንን ማሳደግ እንችላለን ፤ በቀጣይም በእኛ በኩል የተሰጠንን ኃላፊነት በግልፀኝነትና በኃላፊነት ለመስራት ዝግጁ ነን። የብሔር መነሻ የስም ቅጥያ ያላቸው ክለቦች ስያሜ የደቡብ ክልልን መነሻ በማድረግ ስያሜያቸውን እንድስታተካክሉ ፈቃደኛ ሆናቹ። የማትፈፅሙ ከሆነ እኛ በተዘጋጀው ደንብ መሠረት ቀይረን የምናሳውቅ ይሆናል። ከ17 ዓመት በታች ውድድር በተመለከተ ልጆቹ ተማሪዎች ስለሆኑ በሳምንት ልዩነት ከከተማቸው ርቀው መጫወት አይችሉም ብለን ውድድሩን ዳግም ወደ ክልሎች ስንመልስ ከአዲስአበባ ከተማ ውጭ ሌሎች ክልሎች ውድድሩን አፍርሳችኋል፤ ይህም መታረም ይገባዋል።

” ውድድሮች ለማካሄድ የሜዳዎች ግምገም አድርገን በገለፅነው መሠረት ማስተካከያ እርምት መሠረት መስተካከል ይኖርበታል። በተያያዘም ቀጣዩ ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ የሚካሄድ ይሆናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ