የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ትናንት የጀመረ ሲሆን ዛሬም ቀጥሎ አዳማ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የ2011 ቻምፒዮኑ አዳማ ከተማን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገናኘው የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተፈፅሟል።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ በትናንትናው ዕለት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ባዘጋጀው የኮከቦች ሽልማት ሥነ-ስርዓት ላይ ኮከብ ተጫዋች፣ ኮከብ ግብ ጠባቂ እና ኮከብ አሰልጣኝ ሆነው የተመረጡት ሴናፍ ዋቁማ፣ እምወድሽ ይርጋሸዋ እና ሳሙኤል አበራ በስፍራው ለተገኙት ደጋፊዎች ምስጋኔ አቅርበዋል።
ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ገና በጊዜ ነበር። በሁለተኛው ደቂቃ ምርቃት ፈለቀ ያሻማችውን ኳስ ሰናይት በሚገባ ተቆጣጥራ ግብጠባቂዋን አልፋ ያቀበለቻትን እፀገነት ብዙነህ ለውሳኔ በዘገይችበት ቅፅበት ወደ ማዕዘን ወጥቶባታል።
እጅጉን ወደ ተጋጣሚያቸው ሶስተኛ ሜዳ ተጠግው ሲጫወቱ የታዩት አዳማዎች ከርቀት በሚመቷቸው ኳሶች ተጋጣሚያቸው ላይ ግብ ለማስቆጠር ሙከራዎች ቢያደርጉም ስኬታማ መሆን አልቻሉም። በተለይም ሴናፍ፣ ሰናይት እና እፀገነት ሲደርጓቸው የነበሩት ጥረቶች ተጠቃሽ ነበሩ። በ26ኛው ደቂቃ ላይ በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ቡድኑ አዲስ ፈራሚ ምርቃት ፈለቀ ከርቀት የመታችው ኳስ የግቡን የላይኛውን አግዳሚ ለትሞ የወጣበት ሙከራም እጅጉን አስቆጪ ነበር።
ንግድ ባንኮች ከባለሜዳው በተቃራኒ በመልሶ ማጥቃት እና በረጃጅም ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በተለይም በ32ኛው ደቂቃ አንጋፋዋ አጥቂ ረሂማ አመቻችታ ያቀበላቻትን ኳስ ሽታዬ በቀላሉ ያባከነቹ ኳስ አስቆጪ ሙከራ ነበር። ብዙም ሳይቆይ በ38ኛው ደቂቃ ማጥቃቱ ላይ ያመዘኑት አዳማዎች በፈጠሩት ክፍተት ህይወት ዳንጊሶ በረዥሙ ያሻገረችውን ኳስ ሽታዬ ሲሳይ በአግባቡ ተቆጣጥራ ወደ ፊት በመግፋት እና ግብ ጠባቂዋን ጭምር በማለፍ የመታችውን ኳስ ናርዶስ ጌትነት ለማዳን ብትሞክርም ጎል ከመሆን ሳታድነው ቀርታለች። ሽታዬ ሲሳይም የውድድር ዘመኑ የመጀመርያ ጎል አስቆጣሪ መሆን ችላለች።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ባለሜዳዎቹ ይበልጡኑ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም አለመረጋጋት ታይቶባቸዋል። በዚህም ተጨማሪ ክስተት ሳይታይበት በንግድ ባንክ መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች በኳስ ቁጥጥር ድርሻ የተሻሉ የነበሩ ቢሆኑም የጠሩ የግብ እድሎችን ግን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ቀስ በቀስ የበላይነቱን መልሰው መውሰድ የቻሉት አዳማዎችም የጎል ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ከረጅም ርቀት ያገኙትን ቅጣት ምት ሰናይት ቦጋለ አክርራ ወደ ግብ መትታ ግብ ጠባቂው ያዳነችባት እንዲሁም በ60ኛው ደቂቃ ሴናፍ ያደርገችው ሙከራ ተጠቃሽ ነበሩ።
በ62ኛው ደቂቃ አዳማዎች ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን ጎል ማግኘት ችለዋል። በንግድ ባንክ ሳጥን ውስጥ ሰናይት ቦጋለ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ምርቃት ፈለቀ ወደ ግብ ለውጣው ነበር አዳማ ከተማን አቻ ማድረግ ቻለችው።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተጫኑት አዳማዎች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ሳያሳኩ ቀርተዋል። በተቀራኒው ባንኮች ወደ ኃላ አፈግፍገው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በሁለተኛው አጋማሽ ሊጠቀስ የሚችለው ተጨማሪ የግብ ሙከራም በ77ኛው ደቂቃ ላይ የተፈጠረው ሲሆን በቀኝ መስመር በኩል ብርቱካን ያሻማችውን ኳስ ረሂማ ዘርጋው በግሩም ሁኔታ ሞክራ በግብ ጠባቂዋ አስደናቂ የግል ጥረት ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታኮ ሊወጣ ችሏል።
እምብዛም የግብ መከራዎች ያልታየበት የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ እንቅስቃሴ ተጨማሪ ግብ ሳይታይበት 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡
በሊጉ የትላንት መርሐ ግብር ጌዴኦ ዲላ እና አርባምንጭ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል መጠናቀቁ ይታወሳል።
© ሶከር ኢትዮጵያ