ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ ስምንት – ክፍል ስድስት

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም የዛሬው መሠናዶ የስምንተኛው ምዕራፍ ስድስተኛ ክፍልን ይዞላችሁ ቀርቧል።


በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ የእግርኳስ አጨዋወት ሥልቶችን “ተመራጭ” የሚያሰኟቸው በርካታ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ የቀጥተኛ እግርኳስ (Direct Football) አቀራረብ ዘዴም አመዛኝ ተቀባይነት ያገኘባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረው ታይተዋል፡፡ ዘወትር በመሰረታዊ የታክቲክ መርሆዎች ላይ ብቻ ጥብቅ እምነት የማሳደር አክራሪነት (Tactical Fundamentalism) ወደተሳሳተ አመለካከት ያመራል፡፡ ይልቁኑ የእግርኳስ ታክቲኮች በነባራዊና ከባቢያዊ ኹነቶች (Circumstances) እንዲሁም በአንድ ቡድን ውስጥ በሚገኙ ተጫዋቾች የተናጠል ብቃት፣ የአጨዋወት ባህርይና በመሳሰሉት መስፈርቶች ላይ ሊወሰኑ ግድ ይላቸዋል፡፡ የቻርለስ ሪፕ ሃሳብ አቀንቃኞች እርሱ ጥናት ያካሄደባቸው የጨዋታ ቁጥራዊ ትንታኔዎችን አግባብ ባልሆነ መንገድ የመተርጎም አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ 

የእንግሊዛዊው እግርኳሳዊ እሳቤ ደጋፊዎች የአረዳድ እንከን ባያሳዩ እንኳ እርሱ ወደ ጠቅላይ ድምዳሜ የደረሰባቸው የመንስኤ-ውጤት አመክንዮዎች ሙሉ በመሉ ትክክል አልነበሩም፡፡ በታህሣሥ ወር በሮተርሃም (በአንግሊዝ የደቡብ ዮርክሻየር ከተማ) በተካሄደ የሶስተኛ ዲቪዚዮን ጨዋታ ላይ አመቺ የሆነ አቀራረብ እንዴት ተደርጎ ነው በሐምሌ ወር በጓዳላያራ (በምዕራብ ሜክሲኮ የሚገኝ ከተማ) በተከናወነ የአለም ዋንጫ ፍልሚያ ላይ ከተተገበረ ሥልት ጋር በእኩል አይን የሚታየው? እንዴትስ ሆኖ ነው ይህኑኑ ዘይቤ በተለያዩ የአየር ንብረቶች ውስጥ በተመሳሳይ መንገድ ለመጠቀም የሚቻለው? በእግርኳስ ታክቲክ የተካኑ ታላላቅና ብልህ ባለሟሎች ዋነኛ ችሎታ ትክክለኛውን ወይም አስፈላጊውን ታክቲክ አልያም የአጨዋወት ሥርዓት በተገቢው ጊዜ መጠቀም መቻላቸው ነው፡፡ በ1970ው የሜክሲኮ የአለም ዋንጫ ውድድር ይበልጡን በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ ያመዘነ የጨዋታ ዘዴን የተከተለው አልፍ ራምሴይ እንኳ በዚህ ሐሳብ ይስማማል፡፡

ሙሉ በሙሉ ባይሆንም የቻርለስ ሪፕ ቁጥራዊ ትንተናዎች በተለይ ደግሞ በእንግሊዝ የሊግ ጨዋታዎች ላይ ያጠነጠኑት የስታን ኩሊስን የእግርኳስ አጨዋወት ተፈጥሯዊ ስሜት የሚደግፉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ይህ ደመነፍሳዊ ግንኙነት ሁለቱ ሰዎች ፍሬያማ የሥራ መሥተጋብር እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል፡፡ “የእርሱ የጥናት ውጤት ቀደም ሲል ቡድኔ የሚያስተናግዳቸውን በርካታ ግቦች በመቀነስ ረገድ ማስተካከያዎችን እንዳደርግ አንቅቶኛል፡፡ ተጫዋቾቼ ያላቸውን እምቅ አቅም ተጠቅመው የሚፈለገውን ያህል ጎል እንዳያስቆጥሩ ማነቆ የሆነባቸውን የታክቲክ አካሄድ እንድናሻሽልም ረድቶኛል፡፡” ብሏል ኩሊስ ከሪፕ ጋር የመሰረተውን የሃሳብ መግባባት በማስመልከት፡፡ ኩሊስ ከዚህ በተጨማሪ ሪፕ (POMO/Position Of Maximum Opportunity) ብሎ በሰየመው ንድፈ-ሐሳብ እጅጉን ተማርኮ ነበር፡፡ POMO ከግቡ ቋሚ ምሰሶዎች በአጭር ርቀት በሚከወን የማጥቃት ሒደት በርካታ ጎል የማስቆጠር እድሎች የሚፈጠሩበት የሜዳው ክፍል ሲሆን ሪፕ የመሥመር አማካዮች (Wingers) በተደጋጋሚ ወደዚህኛው ክልል እንዲሮጡ ሲያበረታታ ይስተዋላል፡፡ ” ቻርለስ ሪፕ በሃንጋሪው ጨዋታ መዝግቦ ያስቀመጣቸው መረጃዎች ጥልቅና ዝርዝር በመሆናቸው እኔ በእርግጥም የማምንባቸውን መርሆዎች ትክክለኛነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየኛል፡፡ ምናልባት ወደፊት ግራ ሊያጋቡኝ አልያም ሙሉ በሙሉ ከአዕምሮዬ ሊጠፉ የሚችሉ የራሴ ትውስታዎች ላይ እንኳ እምነት እንዳሳድር የተገደድሁት ሪፕ እውነታውን በማያሻማ መልኩ አደራጅቶ ስላስቀመጠ ይመስለኛል፡፡” ይላል ኩሊስ፡፡

የሃንጋሪው የ6-3 ሽንፈት ከማንም በላይ ለአልፍ ራምሴይ ቅዠት ሊሆንበት እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ተጫዋቹ በዚያ ጨዋታ ላይ በቀኝ መሥመር ተከላካይነት ተሰልፎ የእንግሊዝን ሶስተኛ ጎል በፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠሩ ይታወቃል፡፡ ራምሴይ የትኞቹ የሃንጋሪ ግቦች ከረዣዥም ቅብብሎች የተገኙ እንደሆኑ በማስታወሻው አኑሯል፤ የእንግሊዙን ግብ ጠባቂ ጊል ማሪክንም በአሽሙር አዘል ትችት ከመሸንቁጥ ወደኋላ አላለም፡፡ “ተጋጣሚያችን ያደረጋቸው ሁሉም ወደ ጎል የሚሞከሩ ጠንካራ ምቶች በሙሉ ግብ የሆኑለት ገዳም ዕለት ነው፡፡” ሲል ገልጿል፡፡ ነገር ግን ይህ የማጣጣል አስተያየት እንጂ እውነታው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ 

በጨዋታው ሃንጋሪ ሰላሳ አምስት የጎል መኩራዎችን ስታስመዘግብ ተጋጣሚዋ እንግሊዝ ግን አምስት ብቻ ሙከራዎች አድርጋለች። ሃንጋሪ በሁለተኛው አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ሙሉ በሙሉ ከእንግሊዝ ወስዳለች፡፡ በዚያ ላይ ሃንጋሪያውያኑ ማራኪ አጨዋወት አሳይተዋል። አልፍ ራምሴይ የውጭ ሃገራት ዜጎች ላይ ተጸናውቶት የቀረው የአግላይነት ስሜት ታክሎበት ካልሆነ በቀር ይህን ገሃድ የታየ ሐቅ ማድበስበስ የሚቻል አይመስልም፡፡ በአንድ ወቅት ራምሴይ ሞስኮ በሚገኘው ታሪካዊው የቦልሾይ ቴአትር ቤት <ስሊፒንግ ቢውቲ> የተሰኘ የዘመኑ ድንቅ ሲኒማ ላይ እንዲታደም ቢጋበዝም እዚያው በመዲናይቱ ባለው የብሪታንያ ኤምባሲ የመዝናኛ ክበብ ውስጥ በመላው እንግሊዝ ተወዳጅነት ያተረፈውን ተከታታይ የአልፍ ጋርኔት ፊልም እንዳያመልጠው ግብዣውን እምቢኝ ብሏል፡፡ ለሰውየው እንግሊዝና እንግሊዛዊነት ከምንም በላይ መሆኑን ልብ ማለት ሳያሻ አይቀርም፡፡ በተጫዋችነት ያደገበት ክለብ የአጨዋወት ሥልት ከሃንጋሪያኖቹ የጨዋታ ዘይቤ ጋር እምብዛም የማይራራቅ የመሆኑ ነገርም ይሆናል ያን ያህል ያለመደነቅ ስሜት የፈጠረበት፡፡ በቶተንሃም ሲጫወት የፊት መሥመር ተሰላፊዎች ወደኋላ እያፈገፈጉ ክፍተቶች እንዲፈጥሩ ሲበረታቱ አይቷል፡፡ ምናልባትም ራምሴይ እንደ ሌሎች ሰዎች የሃንጋሪያውያንን የታክቲክ አረዳድ ወይም የቴክኒክ ችሎታ ለማወደስ ፈቃደኛ ያልሆነው ለዚህ ይመስላል፡፡ በእርግጠኝነት እርሱ ውበት ላለው እግርኳስ ጨርቁን የሚጥል ሰው አልነበረም፡፡

አልፍ ራምሴይ እንግሊዝን ለብቸኛው ዓለም አቀፋዊ ድሏ አብቅቷትም እርሱ ላይ የሚሰጠው የግምገማ አስተያየት አዎንታዊና አሉታዊ ሃሳቦችን ይዞ የተደበላለቀ ስሜት ማንጸባረቁ ግራ አጋቢ ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል ወደኋላ በመመለስ ልክ ኸርበርት ቻፕማንን እንደሚያስቡ አልያም የ2-3-5 ፎርሜሽንን ትንሳኤ እንደሚያቀነቅኑ ወገኖች የ1966ቱን የዓለም ዋንጫ ስኬት እያወሱ ብዙዎች አልፍ ራምሴይን ከዚያ በኋላ በመላ ሃገሪቱ ለተንሰራፋው የአጨዋወት ዘዴ ሞዴል (Blue Print) አድርገው ይወስዱታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ የተጠቀሰውን ተጻራሪ ሃሳብ ይዘው ራምሴይን የሚሞግቱ አካላት አሉ፡፡ እነዚህኞቹ እንደምንም ብለው የወቀሳ በትራቸውን አሰልጣኙ ላይ የሚያሳረፉ ናቸው፡፡ የእርሱ ጥፋት ይመሥል በጊዜ ሒደት ከሚመጡ የእግርኳስ አጨዋወት እድገቶች ጋር ራሳቸውን ለማዛመድ ከማይሹ ወይም አዕምሮአዊ ብቃት ሳይኖራቸው ራምሴይ ውጤታማ የሆነበትን መላ ብቻ ሙጥኝ የማለት ወግ አጥባቂ የሥልጠና መንገድ ለማስኬድ የሚጥሩትን አሰልጣኞች እንዲበዙ እንዳደረገ የሚያስቡ ናቸው፡፡ በ1966 እንግሊዝ የዓለም ዋንጫውን ብታሸንፍም ለራምሴይ የሚገባውን ክብር ለመቸር ያንገራገሩም አልታጡም፡፡ ግለ ታሪኩን የጻፈው ዴቭ ቦውለር “ነቃፊዎቹ እርሱ በጨዋታ ዙሪያ ለጥቃቅንና ዝርዝር ጉዳዮች የሚሰጠውን ትኩረት ቤተ ሙከራ ውስጥ ለጥናት እንደገባ እንስሳ ያያሉ፡፡ ድርጊቱን ለእግርኳስ ጨዋታ ማራኪ ውበት የሚያላብሰውን ገጽታ እንደሚያጎድልና ወደ ሳይንሳዊ ትንተና እንደሚያወርደውም ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ ይህ እርሱ ጨርሶ የማይስማማበት ጉዳይ አይደለም፤ እንዲያውም ራምሴይ ትችቱን እንደ ሙገሳ ይወስደዋል፡፡ እግርኳስ ለእርሱ የተከታታይ ታክቲካዊ ልምምድ፣ የአዕምሮ ብስለት እና የአካል ብቃት ውጤት ነው፡፡” ይላል፡፡ ይህ ዕምነቱ ራምሴይ የሰውን ሐሳብ ላለመቀበል በችኮነት የሚፈረጅበት መለያ ባህርዩን ለማለዘብ አላገዘው፤ ያም ቢሆን እርሱ ግድ አይሰጠውም፡፡   

አልፍ ራምሴይ በነባራዊ እውነታዎች ላይ ከልቡ የሚያምን ሰው (Realist) ነበር፡፡ ይህ አቋሙ በነሐሴ 1955 ኢፕስዊች ታውንን በአሰልጣኝነት እንደተረከበ በግልጽ ታይቷል፡፡ አርቱር ሮው በስፐርስ ያሰረጸውን የአጨዋወት ዘዴ በኢፕስዊች መተግበር ቢችልም ብዙ በማይጠበቅበትና በደቡብ እንግሊዝ ሶስተኛ ዲቪዚዮን ተወዳዳሪ በሆነ ቡድን ዘንድ የ<Push-And-Run> ሥልት ቦታ እንዳልነበረው ወዲያው መገንዘብ ችሏል፡፡ በኢፕስዊች የመጀመሪያ ጨዋታውን በቶርክዋይ ዩናይትድ 2-0 ቢሸነፍም የነገሮችን ጅምር ቀለል ለማድረግ ሞክሯል፡፡ የ<ኢስት አንግሊያን ዴይሊ ታይምስ> ጋዜጣ ዘጋቢም በጨዋታው ላይ በታዩት የማዕዘን ምቶች ቁጥር እጅግ መደነቁን አውስቷል።

ቀስ በቀስ እንግሊዛዊው አሰልጣኝ በኢፕስዊች እየተሳካለት ሄደ፡፡ ራምሴይ በክለቡ እስከ ታህሳስ መጨረሻ ድረስ ብዙ ለውጦችን ለመፍጠር ቢቸገርም ያኔ የጀመረው ለውጥ ከ1956 በኋላ ለአስር ዓመታት በዘለቁ ሒደታዊ ዕድገቶች ውስጥ ፍሬው በአለም ዋንጫ ውድድር ላይ ታይቶለታል፡፡ ጂሚ ሊድቤተር ባለ ተሰጥኦና ብልህ ከመሃል አጥቂዎች በስተግራ የሚጫወት የፊት መስመር ተሰላፊ (Inside Forward) ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተጫዋቹ የሚስተዋልበት ከፍተኛ የፍጥነት ችግር ምርጥ ብቃቱን እንዳያሳይ ጋሬጣ ሆኖበት ሰንብቷል፡፡ሊድቤተር በ1955 የክረምቱ ዝውውር ወቅት ከራምሴይ በፊት ኢፕስዊችን ያሰለጥን በነበረው ስኮት ደንከን አማካኝነት ለክለቡ ፈረመ፡፡ በአልፍ ራምሴይ የመጀመሪያ አራት ወራት ቆይታም አንዴ ብቻ መሰለፍ ቻለ፡፡ በዚህም ሳቢያ የወደፊቱ የእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወቱ ህልውና ያሳስበው ገባ፡፡ ስለዚህም ወደ ሌሎች ክለቦች ማማተር ጀመረ፡፡ አዲሱ ዓመት ከመግባቱ በፊት ራምሴይ ሊድቤተርን በግራ መስመር (Left Wing) የመጫወት ፍላጎት እንዳለው ጠየቀው፡፡ ተጫዋቹ ፈጣን ባለመሆኑ በመሥመር አማካይነት ለመሰለፍ ፈራ፡፡ የራምሴይ ጭንቀት የነበረው ግን የሊድቤተር ኳስ የመያዝ ብቃት ነበር፡፡ ” የግራ መስመር አማካይ (Left Winger) ሆኜ እንድጫወት አደራ ተጣለብኝ፤ ግን ሚናውን በመወጣቱ ረገድ አልተሳካልኝም፡፡ ከዚያ እንደገና ወደኋላ ተመልሼ ከራሳችን ተከላካዮች ኳስ እንድቀበል ተደረግሁ፤ የተጋጣሚ ቡድን የመስመር ተከላካዮች (Full-Backs) እኔ ያለሁበት ድረስ መጥተው ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርጉብኝ (Mark) አይችሉም፤ ስለዚህም እንዳሻኝ የምንቀሳቀስበት ክፍተት አገኘሁ፡፡ አልፎአልፎ ወደፊት ስገሰግስ በመስመሬ የሚጋፈጠኝን የባላጋራ ቡድን የቀኝ መሥመር ተከላካይ (Right Back) ከክልሉ ውጪ ጥዬው መሮጥ ቻልኩ፡፡ እርሱ (የመሥመር ተከላካዩ) በመሃለኛው የሜዳ ክፍል ማንንም ሳይቆጣጠር ብዙ መቆየት ስለሌለበት እኔኑ መልሶ መከታተል ይጀምራል፡፡ ይህ ደግሞ በሜዳው ቁመት የግራ መስመር ላይ ሰፊ ክፍተት እንድንፈጥር ያስችለናል፡፡ ስለዚህ የመሃል አጥቂያችን ቴድ ፊሊፕስ ወደዚሁ ቦታ እየመጣ በነጻነት ይጫወታል፡፡ ፊሊፕስ የሚንቀሳቀስበት ክፍተት ይፈልጋል፤ ኳስና ነጻ ቦታ ካገኘ ግብ የማስቆጠር ችግር አልነበረበትም፡፡ ሲል ሊድቤተር የቦታና ሚና ለውጡን ውጤት ይናገራል፡፡ 

በ1957 ኢፕስዊቾች ወደላይኛው የሊግ እርከን አደጉ፡፡ የመሃል አጥቂው (Centre-Forward) ሬይ ክራውፎርድ ፖርትስመዝን ለቆ እኛን ተቀላቀለ፡፡ ቀጥተኛው የቀኝ መስመር አማካይ (Orthodox Right Winger) ሬይ ስቴፈንሰንም ከሌይስተር ሲቲ ተዛውሮ መጣ፡፡ ይህን ጊዜ የራምሴይ ዕቅድ ቅርጹን ያዘ፤ ከዚያም 4-2-4 ፎርሜሽንን መተግበር ጀመርን፡፡ ልክ ብራዚል የ1958ቱን ዓለም ዋንጫ ስታሸንፍ እንደተጠቀመችው ፎርሜሽን የእኛም የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር መጠነኛ ሽግሽግ የታከለበትና ከተለመደው 4-2-4 የመሃሉ ክፍል ውቅር ትንሽ ጠምዘዝ ያለ እንጂ ወጥና ዝርጉ አልነበረም፡፡ በብራዚል ማሪዮ ዛጋሎ ከፊት መስመር ተነስቶ ወደኋላ በመመለስ እንደሚጫወተው በኢፕስዊችም ሊድቤተር በተመሳሳይ ኃላፊነት እንዲንቀሳቀስ ተመረጠ፡፡ የተጫዋቹ አነስተኛ ፍጥነት ባለቤትነት ላፈገፈገ ሚና (Deep-Lying Role) አመቺ እንዲሆን አስገደደው፡፡ በዚህ ሁኔታ ምንም እንኳ የአጨዋወት ዘይቤ ልዩነት ቢታይበትም የራምሴይ ቡድን ፎርሜሽን ብራዚል በ1958 ከተገበረችው የ4-2-4 ፎርሜሽን ይልቅ በ1962 የተጠቀመችውን ከወደ መሃሉ የተጣመመ ቅርጽ ከነበረው 4-3-3 ጋር ተመሳሰለ፡፡

“ከተከላካይ ክፍላችን ጀምረን በፍጥነት በማጥቃት እናምናለን፤ አንድ ቡድን ልክ የማጥቃት ሒደቱ በተገታበት ቅጽበት ለጥቃት ተጋላጭ ይሆናል፡፡ በእኔ ሃሳብ በዚህ የሽግግር ሒደት ‘ሶስት ረዣዥም ኳሶች በቂ የቅብብሎች መጠን ነው፡፡’ ብዬ አምናለሁ፡፡” ይላል ራምሴይ፡፡ ሁለቱ ባለሙያዎች (ቻርለስ ሪፕ እና አልፍ ራምሴይ) ተገናኝተው ይወቁ-አይወቁ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም “ሶስት” የሪፕም ምትሃታዊ ቁጥር የመሆኑ ጉዳይ ምናልባትም ያጋጣሚ ላይሆን ይችላል፡፡ 

” የአልፍ ሃሳብ ‘ቁጥራቸው ያነሱ ቅብብሎችን በከወንክ ቁጥር ያልተሳኩ ቅብብሎችን የመፈጸም መጠንህ ይቀንሳል፡፡’ የሚል ነበር፡፡ ሶስት ቀላልና የተሳኩ ቅብብሎችን ማድረግ የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም አስር ተከታታይ ቅብብሎችን ለመከወን ሲሞከር አንደኛው ቢመክን የሒደቱ አጠቃላይ ትስስር ይቋረጣል፡፡ ስለዚህ ሁሌም ሶስተኛውን ቅብብል ወደ ጠንካራ ምት መቀየር በሚያስችልበት ቦታ ላይ ሆኖ መጠበቅ ያሻል፡፡ የያኔዎቹ ቡድኖች  የሚጫወቱት በዚህ መንገድ ስለነበር የአልፍን ፍላጎት መተገብር ብዙም አላዳገተም፡፡” ይላል ሊድቤተር።

ጊዜው የW-M ትልቁ ጉድለት የፎርሜሽኑ መዘውር የሶስት ተከላካዮችን ብቻ መሰለፍ የግድ ማለቱ ነበር፡፡ አንድ በማጥቃት ሒደት ላይ ያለ ቡድን ጥቃቱን የሚከውነው በግራው መስመር ከሆነ የተጋጣሚው ቀኝ መስመር ተከላካይ (Right-Back) የባላጋራውን የግራ መስመር አማካይ (Left Winger) ለመቆጣጠር ወደ እርሱ ቀርቦ ለመከላከል ይጥራል፤ የመሃል-ተከላካይ አማካዩ (Centre-Half) የተቃራኒ ቡድን የመሃል አጥቂ (Centre-Forward) ላይ የቅርብ ክትትል ያደርጋል፤ የግራ መስመር ተከላካዩም (Left Back) በእርሱ መስመር በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ለሚገኘው አማካይ ቀረብ ብሎ ከለላ ይሰጣል፡፡ ነገርግን ተጋጣሚ ቡድን 4-2-4ን ወይም ሌላ ሁለት የመሃል አጥቂዎችን የሚያሰልፍ ፎርሜሽን  የሚጠቀም ከሆነ የመስመር ተከላካዩ ኃላፊነት ሁለተኛውን አጥቂ መቆጣጠር ይሆናል። ፊትለፊት የሚገጥምህ ይህኛው ከለላ (Cover) ብቻ ስለሆነ የሚቆጣጠርህን የመስመር ተከላካይ ካለፍከው ለአጥቂዎች ግብ የማስቆጠር ሰፊ እድል ይፈጠራል፡፡” ይላል ሊድቤተር ራምሴይ የመስመር ተጫዋቾችን ስለሚጠቀምበት ልማድ ሲያብራራ፡፡

በ1961 ኢፕስዊቾች ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን አደጉ፡፡ በቀጣዩ ዓመት ብዙኃኑን የእግርኳስ ቤተሰብ ባስገረመ ሁኔታ የሊጉን ዋንጫ አሸነፉ፡፡ይህን ስኬት ላመጡት አጠቃላይ የቡድኑ ተጫዋቾች መግዣ ሰላሳ ሺህ ፓውንድ ብቻ በቂያቸው ነበር፡፡ በጀቱ ቶተንሃሞች ጂሚ ግሪቭስ ከጣልያን ወደ እንግሊዝ ተመልሶ እንዲጫወት ካወጡት የዝውውር ገንዘብ ሲሶውን እንኳ የማይሞላ መሆኑ እጅጉን አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ <ዘ-ታይምስ> ጋዜጣ ” የኢፕስዊቾችን የውጤታማነት ምስጢር መግለጽ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቀላል ነገሮችን በትክክልና በፍጥነት ይከውናሉ፡፡ ሆኖም በጨዋታ አቀራረባቸው ላይ ከተለመደው መንገድ በተለየ የሚጠቀስ የተጫዋቾች ቴክኒካዊ ክህሎት አይታይም፤ አጨዋወታቸው ቀልብን የሚስብ ውበት አልተላበሰም፤ ፈጽሞ ማራኪ አልነበሩም፡፡ ነገሩ በእንግሊዝ በሚነገረው ታሪክና ምሳሌ አወዳሽ ግጥም ውስጥ እንደተጠቀሰው ገጸ ባህርይ (Honest Labourer) ጠንክሮ በመስራት ብቻ ከሚገኘው ጸጋ መቋደስን ያስታውሳል፡፡” ብሏል በዘገባው መደምደሚያ ላይ፡፡

በዚያ ዘመን የቴሌቪዥን ሥርጭት ተደራሽነት አናሳ በመሆኑ የኢፕስዊቾችን የአጨዋወት ታክቲክ በቀላሉ ለመገምገም ያዳግት ነበር፡፡ የወቅቱ ምርጥ ተከላካዮችም የራምሴይን ቡድን የጨዋታ ሥልት መቋቋም ተስኗቸው ታይተዋል፡፡ የያኔው የፉልሃም ተጫዋች የሚከተለውን ያስታውሳለል፡፡” ሊድቤተር ወደኋላ አፈግፍጎ ይጫወት ጀመር፤ እኔ ራሴ ማንን መቆጣጠር እንደነበረብኝ ጠፋኝ፤ ከመጫወቻ ቦታዬ ወደፊት እንድሄድ እያስገደደኝ ወደ እርሱ ስጠጋ ሊድቤተር በአናቴ ላይ ለክሮውፎርድና ፊሊፕስ የአየር ላይ ኳሶችን ይልክ ጀመር፡፡ ሁላችንም የፉልሃም ተጫዋቾች መደበኛ ቦታችን ላይ መሆናችንን ሳናረጋግጥ ሁለት ግቦች ተቆጠሩብን፡፡ ሃንትንና ኸርስትን ተክተው የገቡት ክሮውፎርድና ፊሊፕስ ብዙም ሳይቆይ ለእንግሊዝ የመጫወት ዕድል አገኙ፡፡” ሲል በጊዜው የፉልሃምና የብሄራዊ ቡድኑ የመስመር ተከላካይ የነበረው ጆርጅ ኮሄን ይገልጻል፡፡

ይሁን እንጂ በቀጣዩ ዓመት ክለቦች ከኢፕስዊች ጋር ሲጫወቱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እየተረዱ ሄዱ፡፡ በ1962ቱ የቻሪቲ ሺልድ ፍልሚያ ስፐርሶች ኢፕስዊቾችን 5-1 ድል አደረጉ፡፡ የለንደኑ ክለብ አሰልጣኝ ቢል ኒኮልሰን ሁለቱን የመስመር ተከላካዮች (Full-Backs) ከመስመሮቻቸው ወደ ውስጥ ገባ ብለው የተጋጣሚያቸውን ሁለት የመሃል አጥቂዎች (Centre-Forwards) እንዲቆጣጠሩ ዕቅድ አወጣ፤ የመሥመር አማካዮቹን (በ2-3-5 ፎርሜሽን ከተከላካይ አማካዩ ግራና ቀኝ የሚሰለፉት ተጫዋቾች <Half Back>) ደግሞ ሊድቤተርና ስቴፈንሰን ላይ የቅርብ ርቀት ጥብቅ ክትትል (Marking) እንዲያደርጉ አዘዛቸው፡፡ ኢፕስዊቾች በሰፊ የጎል ልዩነት ተሸነፉ፡፡ ይህን ያዩ ሌሎች ቡድኖች ተመሳሳዩን አሰላለፍና የቁጥጥር ሥርዓት ተጠቀሙ፡፡ በዚያው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ አልፍ ራምሴይ የእንግሊዝን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት መንበር ከመረከቡ በፊት ክለቡ (ኢፕስዊች ታውን) አስራ አምስት ጨዋታዎች አድርጎ ማሸነፍ የቻለው ሁለቱን ብቻ ሆነ፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡