“የዚህ ዓመት እቅዴ ከቡድኔ ጋር ጥሩ ዓመት ማሳለፍ ነው” ካርሎስ ዳምጠው

ባለፈው የውድድር ዓመት ከጅማ አባቡና ጋር ጥሩ ዓመት አሳልፎ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወልዋሎን በመቀላቀል ቡድኑ በሁለቱም የሊግ ጨዋታዎች አሸንፎ ሲወጣ ጎልተው ከወጡት ተጫዋቾች አንዱ ካርሎስ ዳምጠው ነው።

ከዚህ ቀደም በነገሌ አርሲ፣ መከላከያ፣ አውስኮድ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ጅማ አባቡና መጫወት የቻለው ግዙፉ ተጫዋች ስለ ወቅታዊ አቋሙ እና ስለ ቡድኑ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል ።

ከወልዋሎ ጋር ያለህ የእስካሁኑ ቆይታ ምን ይመስላል?

ከቅድመ ውድድር ጀምሮ በጥሩ ሁኔታ፤ በጥሩ ተነሳሽነት ነው እየሰራን ያለነው በግሌም ጠንክሬ እየሰራው ነው። ከዚ በፊት አብሬ ከሰራሁትና ከማውቀው አሰልጣኝ ጋር ነው እየሰራው ያለሁት። አሰልጣኛችን በሚሰጠኝን መመርያ መሰረት እንደ ቡድን ጥሩ እየሰራን ነው። በግሌም አሰልጣኙ ጥሩ እየረዳኝ እሱ በሚፈልገው መንገድ ጥሩ እየተንቀሳቀስኩ ነው። ለአሁኑ ጥሩ ብቃቴ የአሰልጣኛችን ዮሐንስ ሳህሌ ድርሻ ትልቅ ነው።

በወልዋሎ የአጭር ጊዜ ቆይታህ በተለያዩ ቦታዎች እየተጫወትክ ነው። ያንተ ፍላጎት በየትኛው ቦታ መጫወት ነው?

አሰልጣኜ አምኖብኝ በየትኛውም ቦታ ቢያሰልፈኝ መጫወት እችላለው። ከዚህ በፊት በመስመር ተከላካይ፣ አማካይ ላይ እና አጥቂ ላይ ተሰልፌ ተጫውቻለው። አሰልጣኛችን አምኖብኝ እስካሰለፈኝ ድረስ በየትኛውም ቦታ ላይ መጫወት እችላለው። መጫወት ስራዬ እስከሆነ ድረስ በየትኛውም ቦታ ላይ ደስተኛ ሆኜ ነው የምጫወተው። ደስ የሚለው ነገር አሰልጣኛችን በየትኛውም ቦታ ሲያሰልፈን ማረግ ያለብንም ነገር በጥልቀት ነው የሚነግረን። በዚህ ደሞ እኛ ተጫዋቾች ተጠቃሚ አድርጎናል። በዛም ምክንያት ነው እንደ ቡድን ጥሩ የሆንነው።

የቆሙ እና ከረጅም ርቀት ላይ የሚመቱ ኳሶች ላይ ያለህን አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻልክ ነው…

እንደዚ አይነት ነገሮች ላይ ለማሻሻል የግል ልምምዶች ማድረግ የግድ ነው። ከውጭ ተጫዋቾች የምንወስደው ልምድም አለ፤ እነሱም በግል እንደሚያዳብሩት ይታወቃል። ከዛ በተጨማሪ ግን አሰልጣኛችን እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በጥልቅ ነው የሚያስረዳን። የቆመ ኳስ አመታት ጨምሮ በየትኛው ቦታ ላይ ምን አይነት ምት መምታት እንዳለብን ስለሚያስረዳን ብዙም አንቸገርም። ከዛ ባለፈ ደሞ ሜዳ ውስጥ ለምናረገው ነገር ጥሩ ሞራል ነው የሚሰጠን። በጠቀስካቸው ነገሮች ላይ እንዳሻሽል አሰልጣኜ ስለረዳኝ እና ልምምድ ቦታ ላይ በምንሰራቸው ሥራዎች ነው።

በዚ ዓመት በግልህ ምን አቅደሃል?

የዚ ዓመት እቅዴ ከቡድኔ ጋር ጥሩ ዓመት ለማሳለፍ ነው። ቡድኔ ውጤታማ እንዲሆን የተቻለኝን ለማድረግ እና በተሰለፍኩበት የተሰጠኝን የስራ ድርሻ በአግባቡ መከወን ነው የዚ ዓመት ቀዳሚው እቅዴ።

የወልዋሎ ደጋፊ በመጀመርያው የሜዳ ጨዋታችሁ ስላደረገላቹ አቀባበል እና ቡድኑ ከደጋፊው ጋር ስለፈጠረው ቁርኝት ምን ትላለህ?

እንደሚታወቀው ከቅድመ ውድድር ዝግጅት ቀጥታ ወደ አዲስ አበባ አምርተን ነው በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የተሳተፍነው። ደጋፊያችን የቡድኑን መምጣት በጉጉት ሲጠብቀው ነበር። ሁሉም እንደሚያውቀው ደጋፊው እና ቡድኑ በጣም ጥብቅ ቁርኝት ነው ያለው። ከዛ በተጨማሪ ደጋፊዎቻችን እስካሁን ድረስ ከጎናችን ነው ያሉት ያበረታቱናል። እነሱ ያን ሁሉ ኪሎሜትር አቋርጠው መጥተው በጥሩ መንፈስ ሲደግፉ ስታይ የሥራ ፍላጎትህ ነው የሚጨምረው።


© ሶከር ኢትዮጵያ