ለዓለም ብርሀኑ በህንድ የነበረውን ህክምና አጠናቆ ተመልሷል

በጉልበቱ ላይ ጉዳት ገጥሞት የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ለዓለም ብርሀኑ በህንዱ አፖሎ ሆስፒታል ሲከታተል የቆየውን ህክምና አጠናቆ ተመልሷል፡፡

ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር ካደረገው የወዳጅነት ጨዋታ መልስ ቢሾፍቱ ላይ ከክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ዝግጅት በመስራት ላይ ሳለ በጉልበቱ ላይ ጉዳት ገጥሞት የነበረው ግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሀኑ ጉዳቱን በሀገር ውስጥ ለመታከም ቢሞክርም MRI ከተመረመረ በኃላ ዶክተሮች እና ፊዚዮቴራፒስት ይስሀቅ ሺፈራው ለተሻለ ህክምና ከሀገር ወጥቶ እንዲታከም በሰጡት ምክር ለአስራ አምስት ቀናት ያህል በህንድ አፖሎ ሆስፒታል ህክምናውን ተከታትሏል።

ግብ ጠባቂው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ ህክምናው ይህን ብሏል፡-

“በህንድ ህክምና ሳደርግ አስራ አምስት ቀን ቆይቻለሁ። የገጠመኝ MCI የሚባል የጉልበት ህመም ሲሆን ቀዶ ህክምና የሚያስፈልገው ስላልነበረ ዶክተሮቹ በማሽን ብቻ የተጎዳውን አካል አክመውኛል፡፡ በደንብ ለማገገም ቢያንስ በድምሩ ወር ያህል እረፍት ያስፈልገኛል። ከዛም ፊዚዮቴራፒ ማድረግ እጀምራለሁ። ” ብሏል

ተጫዋቹ በስተመጨረሻ ከአንድ ወር በኋላ መሬት መንካት እና መራመድ የሚጀምር ሲሆን ሙሉ በሙሉ ወደ ሜዳ ለመመለስ ደግሞ ሶስት ወራት ያህል እንደሚፈጅበት ዶክተሮቹ እንደነገሩት ገልጿል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ