በቅርቡ እግርኳስ ፌዴሬሽኑ ሜዳዎች ማሟላት ይኖርባቸዋል ብሎ ያወጣውን መስፈርት አንድም የአዲስ አበባ ቡድን እስካሁን ማሟላት አልቻለም።
በሀገሪቱ በሁለተኛ እርከን ላይ የሚገኘው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ሊጀመር ጥቂት ቀናት እየቀረው ቢሆንም እስካሁን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ቡድኖች በየት ሜዳ እንደሚጫወቱ አልታወቀም። ከዚህ ቀደም በደብዳቤ እንዲሁም ከዛም በኋላ የተጫዋቾች የደሞዝ ጣሪያ ለመወሰን በነበረው ስብሰባ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በተደጋጋሚ ማንኛውም ቡድን የተቀመጡ የሜዳ መሥፈርቶችን ሳያሟላ ጨዋታ እንደማያደርግ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
በዚህም የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ 36ቱ ክለቦች የሚጫወቱበትን ሜዳ ተዟዙሮ በመመልከት የ14 ቡድኖች ሜዳ ለውድድሩ በቂ ባልመሆኑ በአጭር ጊዜ እንዲያስተካክሉ ተነግሯቸዋል። ሆኖም በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ከሆኑት አስሩም የአዲስ አበባ ቡድን ቡድኖች አንድም ቡድን ያስተካከለ ባለመኖሩ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን ውሳኔን የሚፈትን ሆኗል።
ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉት ቡድኖች ተግባራዊ እያደረጉ ባሉበት በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ቡድኖች ይህን አለመተግበራቸው ውድድሩን በአግባቡ ለመምራት እክል ሊሆን እንደሚችል ከግምት በማስገባት አስሩን የአዲስ አበባ ቡድኖች ለማወያየት ዛሬ በ8:00 የፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ጥሪ ተደርጎላቸዎል።
© ሶከር ኢትዮጵያ