“የቡድናችን ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል” ሳምሶን አየለ

የስሑል ሽረው አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ የቡድናቸው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገለፁ።

የስሑል ሽረ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ የቡድናቸው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ እንደደረሰ እና ቡድኑ ችግሮች እንዳሉበት ከትግራይ ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል። ከአስተያየቱ በኋላም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኙ ችግሩ ከጊዜ ወደ ግየጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ገልፀው በጊዜ ካልተፈታ በቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ እንደማይቀር ገልፀዋል።

“በቡድኑ ችግሮች አሉ፤ ተጫዋቾችም ደሞዝ አልተከፈላቸውም። እኔ የእግር ኳስ አሰልጣኝ ነኝ። አሁን ግን ተጫዋቾቹን ማግባባት እና ማስተባበር ነው የያዝኩት። በዚህ ሁኔታ ላይ ካለ ቡድን ደግሞ ውጤት መጠበቅ ስለማይቻል ጉዳዩን የቡድኑ ደጋፊ እና የእግር ኳስ ማኅብረሰቡ ይወቀው። ብዙ ታግሰናል፤ አሁን ግን ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለደረሰ እና እኔም ከዚ በላይ ተጫዋቾቹን ተጭኖ ወደ ሜዳ ማስገባት ይከብደኛል። ” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ