ሪፖርት | አቤል ያለው ፈረሰኞቹን ሦስት ነጥብ አስጨበጠ

በ2ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰበታ ከተማ በአቤል ያለው ብቸኛ ግብ በመርታት የመጀመርያውን ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።

ከጨዋታው መጀመር በፊት ከቀናት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየቱ አሰልጣኝ ወንድምአገኝ ከበደ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነበር ጨዋታው የጀመረው። ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከጉዳት የተመለሰው ሁነኛው ግብ አዳኛቸው ሰልሀዲን ሰኢድንና የክረምቱ አዲስ ፈራሚ ሀይደር ሸረፋን በመጀመሪያ 11 ሲያካትቱ በአንፃሩ ሰበታዎች ደግሞ ዳንኤል አጄ ፣ ወንድይራድ ጌታሁን ፣ ሳቪዮ ካቡና ፣ ሳሙኤል ታዬና ናትናኤል ጋንቹላ በዛሬው ጨዋታ ተጠቅመዋል።

ጨዋታው እንደተጀመረ ሳልሀዲን ሰኢድ ከቀኝ መስመር አጥብቦ በመግባት ባደረገውና ዳንኤል አጄ ባዳነው አስደንጋጭ ሙከራ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እምብዛም ሳቢ አልነበረም።

በአንፃራዊነት በጨዋታው የተሻሉ የነበሩት ጊዮርጊሶች በክረምቱ መቀለን ለቆ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው ሀይደር በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲመራ ተስተውሏል። በተለይም ከሳልሀዲን ሰዐሐድ ጋር የነበራቸው ቅንጅት ጥሩ የሚባል ነበር።

የሁለቱ ተጫዋቾች ጥምረት በተለይ በ14ኛው ደቂቃ ሀይደር ሞክሮ ዳንኤል ያዳነበት እንዲሁም በ36ኛው ደቂቃ ላይ ሳልሀዲን ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጭ በወጣበት ኳሶች ላይ በጎልህ የሚታይ ነበር።

በአንፃሩ ሰበታዎች ከተለመዱበት አጨዋወት ውጭ በተደጋጋሚ በረጃጅም ኳሶች በፍጥነት ወደ አደጋ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፤ በተለይም ፍፁም ገ/ማርያም ባህሩን አሳልፎ ወደ ግብ የላካትና የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ተረባርበው ያወጧት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።

ከሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በፊት በቅርቡ ለበጎ ተግባር ወደ ሀገራችን የሚመጡ ተጫዋቾችን እያስተባበረ የሚገኘው የቀድሞው የፔኤስጂና ኒውካስትል ተጫዋች ፋብሪክ ፓንክሬት በስታዲየም ተገኝቶ ጨዋታውን ከመከታተል ባለፈ ስታዲየሙን በመዞር ከደጋፊዎች ጋር ትውውቅ አድርጓል።

በጨዋታው ምንም እንኳን ከቡድን አጋሮቹ በቂ ድጋፍ ባያገኝም ፍፁም ገ/ማርያም በግሉ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ነበር። በ50ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ ባደረገውና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ በወጣችበት ኳስ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ ጊዮርጊሶች አሁንም የተሻሉ ነበሩ።

በ69ኛው ደቂቃ ፈጣኑ አጥቂ አቤል ያለው ድንገት ሳይጠበቅ ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በደቂቃዎች ሳልሀዲን ሰኢድ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ ወደጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ሰበታዎች በተለይ በ81ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ባኑ ዲያዋራ በጭንቅላት የሸረፋት ኳስ ከፍፁም ገ/ማርያምን ከባህሩ ነጋሽ ጋር አንድ ለአንድ ቢያገናኘውም ፍፁም ኳሱን መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።

ጨዋታው 1ለ0 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ፈረሰኞቹ የመጀመሪያ ድላቸውን ማሳካት ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ