ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አቃቂ ቃሊቲ ከሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ሦስተኛ ጨዋታ ዛሬም ቀጥሎ በአዲስ አበባ ስታዲየም አቃቂ ቃሊቲን ከሀዋሳ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ከታችኛው ሁለተኛ ዲቪዚዮን የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ያጠናቀቀው እና በሊጉ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደረገው አቃቂ ቃሊቲ ሳይጠበቅ ገና በጨዋታው ጅማሬ በ2ኛ ደቂቃ ላይ የሀዋሳዎች አጥቂ መሳይ ተመስገን የግል ብቃቷን እና ፍጥነቷን ተጠቅም ከርቀት ባስቆጠረችው ጎል መመራት ጀምረዋል።

ፈጥኖ በጨዋታው ጎል ይቆጠር እንጂ ብዙም ሳቢ ያልነበረው ጨዋታ አልፎ አልፎ በሚደረጉ የጎል ሙከራዎች የጨዋታውን እንቅስቃሴ ለመለወጥ በሁለቱም በኩል ጥረቶች ተደርገዋል። በ15ኛው ደቂቃ የአቃቂዋ የመስመር አጥቂ ሠላማዊት ኃይሌ ከቀኝ መስመር ከርቀት የመታችውን ግብጠባቂዋ ዓባይነሽ ኤርቄሎ ያወጣችባት ኳስ በአቃቂዎች በኩል የተፈጠረ የመጀመርያ የጎል አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

የመሳይን ፍጥነት ለመቆጣጠር ቢቸገሩም አቃቂዎች እንደ ቡድን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መልካም ነበር። 20ኛው ደቂቃ የሀዋሳዋ ነፃነት መና ተከለካዮችን በማለፍ ከቀኝ መስመር ኳሱን አሻግራ መሳይ ተመስገን በግራ እግሯ ደገፍ አድርጋ የመተችው ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶባታል።

እምብዛም የማጥቃት ሽግግሩ ላይ መቆራረጥ የሚታይበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በክፍት ሜዳ ጎል ከማስቆጠር ይልቅ በቆሙ ኳሶች ጎል ፍለጋ በተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል። 25ኛው ደቂቃ ሳይጠበቅ በአቃቂ በኩል ፀባኦት መሐመድ ከርቀት ወደ ጎል የመታችውን ግብጠባቂዋ ዓባይነሽ እንደምንም ወደ ውጭ አውጥታባታለች።

ከእረፍት መልስ የቀጠለው ጨዋታ ከመጀመርያው አጋማሽ አቃቂዎች በተሻለ በሀዋሳ ላይ ብልጫ መውሰዳቸው ውጤታማ አድርጓቸው በ57ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ የተጣለላትን ከተከላካዮች ፈጥና በመግባት ኳሱን ከግብጠባቂዋ ዓባይነሽ አንጠልጥላ አቃቂን አቻ ማድረግ የቻለችበትን ሰላማዊት ጎሳዬ ጎል አስቆጥራለች።

መሳይ ላይ ትኩረት ያደረገው የሀዋሳ ከተማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሌላ አማራጭ አጥቂ ፍለጋ የቀድሞ ተጫዋቹን የመለሰው አሰልጣኝ ዮሴፍ አጥቂዋ ዓይናለም አሳምነውን ቀይሮ ካስገባ በኋላ መሻሻልን አሳይቶ 64ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት በአንድ ሁለት ቅብብል ዓይናለም ወደ ፊት ይዛ የሄደችውን ኳስ መሳይ ተቀብላ በግራ እግሯ የመታችውን ግብጠባቂዋ ሺብሬ ካንኮ እንደምንም የመለሰችውን በድጋሚ ዓይናለም አግኝታ ወደ ጎል ብትመታውም የግቡ አግዳሚ መልሶባታል።

ሀዋሳዎች የማሸነፊያ ጎል ፍለጋ በተደጋጋሚ ወደ አቃቂ የግብ ክልል ቢደርሱም የማጥቃት መንገዳቸው ግልፅ ባለመሆኑ ምክንያት ብዙም የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። በአንፃሩ አቃቂዎች ለውድድሩ አዲስ በመሆናቸው ከልምድ አኳያ ክፍተት ቢኖርባቸውም ከእረፍት መልስ አሰልጣኝ አብዱሬ ቀይረው ያስገቧቸው ተጫዋቾችም ሆኑ ቡድኑ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አድርገዋል።

በመጨረሻም በጨዋታው መጠናቀቂያ ከቅጣት ምት የተገኘውን ኳስ መሳይ ተመስገን በቀጥታ ወደ ጎል መትታው የግቡ አግዳሚ የመለሰው ኳስ ሀዋሳን አሸናፊ ማድረግ የምትችል የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። ጨዋታውም በ 1–1 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ