በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከጅማ አባ ጅፋር አቻ ተለያይቷል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
“በእግርኳስ ከባዱ ነገር ጎል ማግባት ሳይሆን የግብ እድሎችን መፍጠር ነው” ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለጨዋታው
“በእግርኳስ ጨዋታ ውስጥ ከባዱ ነገር ጎል ማግባት ሳይሆን የግብ እድሎችን መፍጠር ነው። ይህን ነገር በቀጣይነት ማስቀጠል ከተቻለ ነገሮች ባሉበት አይቀጥሉም፤ የተሳቱትን ኳሶች መጠቀም ይቻላል። ስለዚህ ጨዋታው ከዛ አንፃር ቢታይ የተሻለ ይሆናል።”
ስለመከኑ የግብ እድሎች
“የእኛ ሥራ ወደ ጎል እንዴት መድረስ እንደሚችሉ ማሳየት እንጂ ጎል ጋር ሲደርሱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መንገር አይደለም። እድሉ ከተገኘ በኋላ በዚህ በኩል ምታው ብለን ማለት አንችልም። ይህ ውሳኔ በተጫዋቾቹ በራሳቸው ሁኔታ የሚወሰን ነው።”
“ጨዋታው ወደ አንድ ሜዳ አድልቶ የተደረገ ነበር” ጳውሎስ ጌታቸው – ጅማ አባ ጅፋር
” ዛሬ የገጠምነው ቡድን ብዙ ደጋፊ ያለውና ከሽንፈት የመጣውን ቡናን ነበር። ከጨዋታው በፊት ከተጫዋቾቼ ጋር በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ኳሱን እንዲይዙ እንደምንፈቅድላቸው ተነጋግረን ነበር። ጨዋታው በተለይ ወደ አንድ ሜዳ አድልቶ የተደረገ ነበር፤ ያገኘናቸውን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻልንም እንጂ ጨዋታውን አሸንፈን ልንወጣበት የምንችልበት አጋጣሚዎች ነበሩ።”
© ሶከር ኢትዮጵያ