ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የሔለን እሸቱ ሐት-ትሪክ ለመከላከያ ሦስት ነጥብ አስገኝቷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት አራተኛ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲካሄድ መከላከያ በሔለን እሸቱ ሦስት ጎሎች አአ ከተማን 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ፍፁም የበላይነት ወስደው እንደመጫወታቸውና እንደ አአ ከተማ ለጨዋታው ተዳክሞ መቅረብ መከላካያዎች በርከት ያሉ ጎሎችን አስቆጥረው ማሸነፍ በቻሉ ነበር። ለመከላከያ አዲስ ፈራሚ የሆነችው አይዳ ዑስማን በሁለት አጋጣሚዎች በተመሳሳይ እንቅስቃስቃሴ የተጣለላትን ኳስ ተጠቅማ በፍጥነት ወደ ጎል በመግባት ጎል መሆን የሚችሉ እድሎችን ብታገኝም በአአ ከተማ በግብ ጠባቂ ሥርጉት ተስፋዬ የግል ጥረት መክኖባታል። 

አይዳ ያመከነቻቸው ዕድሎች በተሻለ አቋቋም ለሚገኙት የቡድን አጋሮቿ ባለመስጠት የፈጠረችውን ስህተት አርማ በጥሩ ሁኔታ ለመዲና ዐወል ያቀበለቻትን መዲና ብቻዋን ከግብጠባቂዋ ስሥርጉት ጋር ተገናኝታ አገባች ሲባል በግቡ አናት ላይ የሰደደችው ኳስ መከላከያን መሪ ማድረግ የሚችሉ በጨዋታው አስር ደቂቃዎች ውስጥ የተሞከሩ ግልፅ የጎል ዕድሎች ነበሩ።

ብዙም ያልተደራጀው እና በቂ ዝግጅት እንዳላደረገ በእንቅስቃሴው የሚታየው አአ ከተማ የመከላከያን አጨዋወት ለማበላሸት ካልሆነ በቀር የራሱን አጨዋወት በመከተል የጎል እድል ለመፍጠር ተቸግሯል።

ብልጫ ወስደው መጨዋታቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች በ14ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ በሚጣልላት ኳስ ፈጥና ወደ ጎል የምትገባው አይዳ በሚገርም ሁኔታ ከግብጠባቂዋ ስሥርጉት ጋር ተገናኝ ያመከነችው፣ በ17ኛው ደቂቃ መዲና ዐወል ከመሐል ሜዳ ተከላካዮችን ደጋግማ በማለፍ ወደ ሳጥን ውስጥ ገብታ ወደ ጎል የመታቸውን ኳስ ስራ በዝቶባት የዋለችው ግብጠባቂዋ ስሥርጉት ተስፋዬ እንደምንም ያወጣችባት እንዲሁም 23ኛው ደቂቃ መዲና ዐወል ከቀኝ መስመር በጥሩ መንገድ ገብታ ነፃ አቋቋም ለምትገኘው አረጋሽ አሻግራላት ለጎሉ 2 ሜትር ርቀት ደግፍ አድርጌ አስቆጥራለው ብላ ወደላይ የላከችው ኳስ በመከላከያ ያልተጠቀሙባቸው የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ናቸው።

በተወሰነ መልኩ እየተረጋጉ የመጡት አዲስ አበባዎች ብዙም የተለየ እንቅስቃሴ ባያሳዩም 40ኛው ደቂቃ ቱቱ በላይ ለአሥራት ዓለሙ አቀብላት ወደ ጎል የመታቸው እና ግብጠባቂዋ ታሪኳ ያዳነችው ለአአ ከተማዎች በጨዋታው የፈጠሩት የመጀመርያ እና የመጨረሻው የጎል አጋጣሚ ነበር።

ከእረፍት መልስ ያጎኙትን የጎል አጋጣሚ ያለመጠቀም ችግር በሚገባ አስተካክለው የተመለሱት መከላካያዎች በአንድ ደቂቃ ልዩነት በአአ ከተማ ተከላካዮች መዘናጋት አግኝተዋል። 54ኛው እና በ55ኛው ደቂቃ ሁለት ፈጣን ጎሎች በዕለቱ ጥሩ ስትንቀሳቀስ በነበረው የቡድኑ አምበል ሔለን እሸቱ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው ሁለት ለዜሮ መምራት ችለዋል። ብዙም ሳይቆይ ሌላ ሦስተኛ ጎል 60ኛው ደቂቃ በአአ ከተማ የግብ ክልል ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሔለን እሸቱ ለቡድኗ ሦስተኛ ለራሷ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ጎል አስቆጥራለች።

ከጎሉ መቆጠር በኃላ አአ ከተማዎች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የተሻለ ለመንቀሳቀስ እየሞከሩ ባለበት ወቅት አሰልጣኟ ቀይራ ያስገባቻትን ተጫዋች ብዙም ሳትቆይ በድጋሚ ቀይራ ማስወጣቷ አግራሞትን ጭሯል።

መከላከያዎች ሌሎች ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችሎ ግልፅ ዕድሎችን ቢያገኙም በዕለቱ ጥሩ መንቀሳቀስ ብትችልም ዕድል ከእርሷ ጋር ያልነበረችው አይዳ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። በመጨረሻም በመከላከያዎች በፍፁም የበላይነት በመውሰድ 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ጨዋታው ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ