የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማሮውን ካደረገ ሁለተኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል። ከቅዳሜ እስከ ትላንት በተካሄዱ ጨዋታዎች ወልዋሎ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማ ሁለተኛ ሽንፈትን ቀምሷል፤ ሲዳማ ቡና፣ ባህር ዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለድል መሆንም ችለዋል። እኛም ከሳምንቱ ጨዋታዎች የተመለከትናቸውን ዐቢይ ጉዳዮች በዚህ መልኩ ቀርበዋል።
1. ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች
የ2ኛ ሳምንት ፕሪምየር ሊግ በተለያዩ ከተሞች ሲካሄዱ በተለያዩ መመዘኛዎች ትኩረት የሚስቡ ተጫዋቾች ተስተውለዋል።
– በጎንደር ዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ድሬዳዋ ከተማ ላይ የግብ ናዳ ሲያወርድ ሙጂብ ቃሲም በግሉ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል። ተጫዋቹ ከተከላካይነት ወደ አጥቂት ከተሸጋገረ በኋላ በሒደት ወደ አስፈሪ አጥቂነት የተሸጋገረ ሲሆን ባለፈው የውድድር ዓመት በሁለት ጎሎች ያጣውን የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪን ክብርን ዘንድሮ ለማስመለስ የቆረጠ ይመስላል። በአዳማ ከተማ ዋንጫ እንዲሁም የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ላይ ጎሎች ለማስቆጠር ያልተቸገረው ሙጂብ ከወዲሁ ሐት-ትሪክ በመስራት የሊጉ የጎል መንገድ ማግኘት ችሏል።
– በተመሳሳይ ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ሽመክት ጉግሳ ቀሪዎቹን ሁለት ግቦች ማከል ችሏል። የመስመር ተጫዋቹ ዐምና በፋሲል ወጥ አቋሙን ማሳየት የቻለ ሲሆን ዘንድሮም የቡድኑ ሁነኛ የማጥቂያ መሳርያ መሆኑን በዚህ ሳምንት ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች እና አመቻችቶ ባቀበለው አንድ ኳስ አስመስክሯል።
– ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሚተማመኑበት የፊት መስመር ተሰላፊያቸው ሳልሀዲን ሰዒድ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በቋሚነት ክለቡን በጉዳት ለማገልገል እየተቸገረ ይገኛል። ከአስደናቂ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቆይታ በኃላ የመጀመሪያ ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ በጉዳት ያሳለፈው ሳላ በድጋሚ አሁንም ቡድኑ ሰበታን 1ለ0 በረቱበት ጨዋታ የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት አጋጥሞታል። ይህም ዐምና ምንም እንኳን ጠንካራ የመከላከል ሪከርድ የነበረው ቡድን ግብ በማስቆጠር ረገድ ችግሮች እንደነበሩበት መታየቱ እና ዘንድሮው ከወዲህ በርከት ያሉ የፊት መስመር ተሰላፊ ተጫዋቾች በጉዳት ላይ ከመገኘታቸው ጋር ተዳምሮ ቡድኑ በቀጣይ ይህን ክፍተት በመድፈን ከጨዋታዎች ውጤትን ይዞ ለመውጣት አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅሆቭ ከባድ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።
– በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ የወልዋሎ ስብስብ ውስጥ በሊጉ በመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ካርሎስ ዳምጠው በ2007 በብሔራዊ ሊጉ ለነገሌ አርሲ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳየቱን ተክሎ መከላከያን ቢቀላቀልም በሁለት ዓመት የጦሩ ፕሪምየር ሊጉን በቀላሉ መልመድ አልቻለም። ቀጥሎም በመቀለ 70 እንደርታ ግማሽ ዓመት ቢያሳልፍም በሊጉ ተፅዕኖ መፍጠር ተስኖት ቢስተዋልም አሁን በወልዋሎ ዳግም የተወለደ ይመስላል። በአዲስአበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ላይ መጫወት እንደሚችል ያስመሰከረው ግዙፉ ካርሎስ በሊጉ ደግሞ በፊት አጥቂነት በመጀመረባቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ በጨዋታ አንድ በፍፁም ቅጣት ምት ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከወልዋሎ ጋር ስኬታማ ጊዜያትን እንደሚያሳልፍ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል።
– ሌላው ከተጫዋቾች ጋር በተያያዘ ትኩረት ሳቢ የነበረው የሲዳማ ቡና ተጠባባቂ ተጫዋቾች ጉዳይ ነው። በሲዳማ ቡና እና ስሑል ሽረ መካከል በዝግ በተደረገው ጨዋታ ተጫዋቾቹ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይረው ለመግባት በሚያሟሙቁበት ወቅት ከጎሉ ጀርባ ሲፀዳዱ ተስተውሏል። ሁኔታው ስታዲየሙ ለተመልካች ዝግ ሆኖ ጨዋታው ከመከናወኑ ጋር በተያያዘ በግድ የለሽነት የተከናወነ እንደሆነ ቢገመትም በስታዲየሙ በቂ የመፀዳጃ ቤት አለመኖር እና የተጫዋቾች ለግጥሚያ እና ለእግርኳሱ ክብር አለመስጠትን ቁልጥ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
2. አዲስ አበባ ስታዲየም እና ምክንያታዊ ያልሆነው የትኬት ዋጋ ጭማሪ
ከሰሞኑ እጅግ በጣም መነጋገሪያ የነበረው የአዲስአበባ ስታዲየም መግቢያ ዋጋ ጭማሪ ጉዳይ ኡሉታዊ ተፅዕኖዎችን ይዞ ብቅ ሳይል አልቀረም።
ለወትሮም ቢሆን በጨዋታ ቀን በኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሲጨናነቁ የሚስተዋለው የአዲስአበባ ስታዲየም ጊዜውን ካልጠበቀው የዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ በተወሰኑ በተለይ 100% ጭማሪ በታየባቸው የመቀመጫ ክፍሎች በኩል የሚገቡ የተመልካቾች ቁጥር መቀነስ ስለማሳየቱ የሁለቱን ቡድኖች የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ የተመለከተ በቀላሉ ሊታዘብ የሚችለው እውነታ ነው። ይህንን አሉታዊ ሁኔታ ለመቀልበስ ክለቦቹ በፍጥነት ጉዳዩን ማጤን ይኖርባቸዋል።
በተመሳሳይ ላለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ስታዲየም በጨዋታ ቀን የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ይሰጥ የነበረው የጠብታ አምቡላንስ አገልግሎት ምንም እንኳን ኮንትራቱ መቋረጡን ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ግልፅ ባልሆኑበት ሁኔታ በ2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አባላት ሲሰጥ ለመታዘብ ችለናል። ይህም ሁኔታ ሌላኛው ትኩረት የሳበ አጀንዳ ነበር።
3. የተሸነፉ ቡድኖች ምክትል አሰልጣኞችን በድህረ ጨዋታ አስተያየት
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገራችን በተለይም ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መጠናቀቅ በኋላ አጠር ያሉ ድህረ ጨዋታ ቃለመጠይቆች እየተለመዱ መጥተዋል። ነገርግን ከተለመደው አሰራር ውጭ ቡድኖች ሲያሸንፉ በዋና አሰልጣኞች በአንፃሩ ሲሸነፉ ደግሞ በምክትል አሰልጣኞቻቸው በድህረ ጨዋታ አስተያየት ላይ የመወከላቸው ነገር ያልተፃፈ ህግ እስኪመስል እየተለመደ መጥቷል።
ለማሳያነትም በዚህ ሳምንት ሽንፈት ያስተናገዱት ስሑል ሽረ እና ወላይታ ድቻ በምክትል አሰልጣኞቻቸው በኩል ድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቅ መከወናቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ስለመሆኑ ለማሳያነት ቀረቡ እንጂ በሌሎች ጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚታይ ሁነት ነው።
ከዚህ ቀደም ከዚህ በባሰ መልኩ ቡድናቸው ሽንፈት ሲያስተናግድ የመገናኛ ብዙሃን አባላትን ጥሎ መሄድ የተለመደ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ደግሞ ምክትል አሰልጣኞችን መወከል ሰሞነኛ ፋሽን እየሆነ መጥቷል።
ቡድን ሲሸነፍ በኩራት ስለቡድን አስተያየት መስጠት ሲሸነፍ ደግሞ የሚኖሩትን ወቀሳዎችን ሽሽት ኃላፊነቶችን ወደ ሌላ አካል በማሸሽ ራስን ከተጠያቂነት ለማዳን የሚደረግ ጥረት ለማንም የሚበጅ አይደለምና በሽንፈቶች ውስጥ ቢሆን ሁኔታዎችን ተጋፍጦ ማስተካከል እንጂ ከሚድያ በመሸሽ የሚደረገው ድብብቆሽ የሚበጅ አለመሆኑን ሊረዱት ይገባል።
4. ክለብ ትኩረት
– በበርካታ አስተዳደራዊ ውጥንቅጦች የተተበተበው ጅማ አባ ጅፋር በሊጉ ጅማሮ ከበርካታ ችግሮች ጋር እየታገለ ቢገኝም በሊጉ ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎችን ሁለት ነጥብ ማሳካት ችሏል። በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ከውጭ ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች መጠቀም ካለመቻሉና ሜዳቸው ቅጣት ላይ በመሆኑ ጨዋታዎችን ከሜዳ ውጭ ለማድረግ መገደዱን ተከትሎ በጨዋታዎች ነጥብ ለማስመዝገብ ይቸገራል ቢባልም በሁለቱም ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ ነጥብ ማስመዝገብ ችሏል። በቀጣይም ቡድን አስተዳደራዊ ጉዳዮች በወቅቱ የሚፈቱ ከሆነ ቡድኑ የብዙዎች ግምት ባፋለሰ መልኩ የተሻለ የውድድር ዘመን ጅማሮን ሊያደርግ እንደሚችል ይጠበቃል።
– ዐምና ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደጉት ሰበታ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ እስካሁን በሊጉ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማስመዝገብ አልቻሉም። ሰበታ ከተማ በመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈትን ሲያስተናግድ ወልቂጤና ሆሳዕና አንድ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተው አንድ ነጥብ ማሳካት ችለዋል ።
በዐቢይ ኮሚቴው ውሳኔ መሠረት በሜዳቸው ጨዋታ እያደረጉ የማይገኙት ወልቂጤ ከተማና ሰበታ ከተማ ለሊጉ አዲስ አዳጊ ቡድኖች በተለይ የመጀመሪያ አመት የሊጉ ቆይታ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የደጋፊዎቻቸውን እግዛ አለማግኘታቸው አይነተኛ ተፅዕኖ ስለመፍጠሩ ለማስተዋል ይቻላል። ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማሳካት አልመው በቀጣይ ሦስተኛ ሳምንት ሀዲያ ወደ ድሬዳዋ አቅንቶ ድሬዳዋን ይገጥማል። ወልቂጤ በአቢዮ ኤርሳሞ ፋሲልን ሲያስተናግድ ሰበታ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም አዳማ ከተማን የሚገጥም ይሆናል።
5. ውብ ጎሎች
ከወትሮው በተለየ 2ኛ ሳምንት ፕሪምየር ሊግ በርከት ያሉ ማራኪ ግቦች የተስተናገዱበት ነበር። በተለይም ግቦቹ የግል ብቃት እንዲሁም የቡድን ስራ የታየባቸው መሆኑ ሳምንቱን አስደናቂ ያደርገዋል።
በተለይም ፍፁም ዓለሙ ባህር ዳር ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ ባደረጉት ጨዋታ ከሳሙኤል ተስፋዬ የተቀበለውን ኳስ ከግራ ሳጥን ጠርዝ ጀምሮ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማለፍ ያስቆጠራት፣ ካርሎስ ዳምጠውና አቤል ያለው ከግብ ክልል ጠርዝ አክርረው በመምታት ያስቆጠሯቸው፣ የአዲስ ግደይ የውድድር ዓመቱ ግሩም የቅጣት ምት ጎል እንዲሁም ሙጂብ ቃሲም ከራሳቸው የሜዳ አጋማሽ አስከ ተቃራኒ የግብ ክልል ድረስ እየነዳ በመሄድ ያስቆጠራት ኳስ ተጠቃሾች ናቸው።
6. ዐቢይ ኮሚቴ
ዘንድሮ ሊጉን የማስተዳደር ስልጣኑን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የተረከበው ዐቢይ ኮሚቴ ከአሁኑ የሚያስመሰግኑ ተግባራትን በመፈፀም ላይ ይገኛል።
በተለይም በዚህ ሳምንት በብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል ምክንያት በወጣለት መርሃግብር መሠረት ጨዋታቸውን ማካሄድ ያልቻሉት ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታቸውን እንደቀደመው ጊዜ በቀሪ ተይዞ ከማካሄድ ይልቅ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን እንዲካሄድ በማድረግ በቀጣይ ሳምንት መርሃግብሮች ላይ መፋሰለሶች እንዳይኖሩ ሁኔታዎችን አሸጋሽገው ለመሄድ ያደረጉት ጥረት አድናቆት የሚቸረው ነወ።
© ሶከር ኢትዮጵያ