የሊጉ መሪ ወልዋሎ እና ስሑል ሽረን የሚያገናኘው ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
የመጀመርያው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፈው በሁለተኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና በሰፊ ልዩነት የተሸነፉት ስሑል ሽረዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻሻሎች ቢያሳዩም የቡድኑ የመከላከል አቅም አሁንም የቡድኑ ደካማ ጎን ነው።
በሁለቱም መስመሮች ፈጣን የመስመር ተጫዋቾች የያዙት እና የመስመር ተከላካዮቻቸው በማጥቃቱ ላይ የሚያሳትፉት ስሑል ሽረዎች እንደባለፉት ጨዋታዎች ሁሉ በነገው ጨዋታም በተለመደው መንገድ ያጠቃሉ ተብሎ ሲጠበቅ በመሃል የመከላከል ጥምረት ላይ የተጫዋቾች ለውጥ ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ ነው።
በጨዋታው ከባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ብዙ የተጫዋቾች ለውጥ ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁት ስሑል ሽረዎች በዚህ ጨዋታ የአጥቂያቸው ሳሊፍ ፎፋና መሰለፍ አጠራጣሪ በመሆኑ የፊት መስመር ለውጥ ይጠበቃል። በአንፃሩ ባለፈው ሳምንት በግል ጉዳይ ወደ ሃዋሳ ያላቀናው አማካዩ ኃይለአብ ኃይለሥላሴ እና በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በሥራ ፍቃድ መጓተት ምክንያት ያልተሰለፈው ተከላካዩ አደም ማሳላቺ ቡድኑን ተቀላቅለዋል።
ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፈው ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች የተጫዋቾች ተፈጥሯዊ ሚና በመቀያየር ሁለቱም ጨዋታዎች አሸንፈው በውጤት ደረጃ ጥሩ ደረጃ ላይ ቢሆኑም ከተጋጣምየሚያቸው እኩል በርካታ ክፍተቶች አሉባቸው።
በሁለቱም ጨዋታዎች በረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት ጥረት ያደረጉት ቢጫ ለባሾቹ በአማካይ ክፍል ላይ ከፍተኛ የሆነ የፈጠራ አቅም እጥረት ቢታይባቸው በሁለተኛው ሳምንት በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሰለፉት ሁለቱ ወሳኝ አጥቂዎቻቸው ኢታሙና ኬይሙኔ እና ጁንያስ ናንጋጂቦን በድጋሚ ማግኘታቸው ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው።
በሳሙኤል ዮሐንስ ፣ ፍቃዱ ደነቀ እና ገናናው ረጋሳ የሚመራው የቡድኑ የአማካይ ስፍራ በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ላይ ጉልህ ድርሻ ባይኖራቸውም ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን በመስጠት ቡድኑ የተረጋጋ የመከላከል ቅርፅ እንዲኖረው በመወጣት ይገኛሉ።
ወልዋሎዎች በዚ ጨዋታ በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም። በአንፃሩ በሁለተኛው ሳምንት ቡድናቸውን ያላገለገሉት ኢታሙና ኬይሙኔ እና ጁንያስ ናንጋጂቦ ወደ ቋሚ አሰላለፉ ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እርስ በርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ድል አስመዝግበዋል። በአጠቃላይ አራት ጎሎች ሲቆጠሩ ሁለቱም ቡድኖች ሁለት ሁለት አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ስሑል ሽረ (4-2-3-1)
ምንተስኖት አሎ
አብዱሰላም አማን – ዮናስ ግርማይ – አደም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ
ሙሉዓለም ረጋሳ – አክሊሉ ዋለልኝ
ዲዲዬ ለብሪ – ያስር ሙገርዋ – ዓብዱለጢፍ መሐመድ
ሳሊፍ ፎፋና
ወልዋሎ (4-2-3-1)
ኬይታ ዓብዱልዓዚዝ
ምስጋናው ወልደዮሐንስ – ዓአይናለም ኃይለ – አሞስ አቼምፖንግ – ሄኖክ መርሹ
ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሐንስ
ኢታሙና ኬሙይኔ – ካርሎስ ዳምጠው – ራምኬል ሎክ
ጁንያስ ናንጋጂቦ
© ሶከር ኢትዮጵያ