ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

ከ3ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል በሁለት ጨዋታ ሽንፈት ያስተናገደው እና ወደ አሸናፊነት ለመመልስ የሚያልመው ሰበታ ከተማን በ4 ነጥቦች ጥሩ ጅማሮ ካደረገው አዳማ ከተማ ጋር የሚያገናኘው ጨዋታን በተከታዩ መልኩ ዳሰነዋል።

በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት በወልዋሎ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ያስተናገዱት ሰበታዎች አስከፊ አጀማመራቸውን ለማስተካከል ከሦስተኛው ሳምንት የአዳማ ከተማ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት የግድ ይላቸዋል።

ሰበታዎች በተከታታይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረጎቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ ምንም እንኳን መሀል ለመሀል የግብ እድሎችን ለመፍጠር የተሻለ አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን ቢይዙም በተለይ በመጀመሪያው ጨዋታ ወደ ኃላ የተሰበሰበውን የወልዋሎ የመከላከል አደረጃጀት ለማስከፈት በእጅጉ ተቸግረው ተስተውለዋል። ይህንን ለማድረግ በሚቸገሩበት ወቅት በቀጥተኛ አጨዋወት ወደፊት ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት በተለያዩ ምክንያቶች በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ በፊት አጥቂነት ፍፁም ገ/ማርያምን መጠቀማቸው ቡድኑ ለዚህ አጨዋወት ውጤታማ ለመሆን ከፊት የሚፈልገውን የመጀመሪያ አየር ላይ ኳሶችን በማሸነፍ ረገድ በተለይም ከግዙፍ የመሀል ተከላካዮች ጋር በሚደረጉ ፍልሚያዎች የፍፁም የማሸነፍ ንፃሬ አነስተኛ በመሆኑ ቡድኑ እየተቸገረ ይገኛል።

በመከላከሉ ረገድም የመጀመሪያ ተመራጮች የሆኑት አንተነህ ተስፋዬን በረጅም ጊዜያት ጉዳት እንዲሁም አዲስ ተስፋዬን በመጀመሪያ ጨዋታ በተመለከተው ቀጥታ ቀይ ካርድ ያጡት ሰበታዎች በጋራ ብዙም የጨዋታ ጊዜ ባላሳለፉት ወንዲፍራውና ሳቪዮ ጥምረትም አስተማማኝነት ላይ አሁንም ጥያቄዎች ይነሳሉ። ምናልባት ከቅጣት መልስ አዲስን ማግኘታቸው የኋላ ክፍሉን ለማጠናከር አጋዥ ይሆናቸዋል ተብሎም ይጠበቃል።

በሰበታ በኩል ተከላካዩ የአንተነህ ተስፋዬን በጉዳት የማያሰልፍ ሲሆን አዲስ ተስፋዬ ከቅጣት መልስ ግልጋሎት የሚሰጥ ይሆናል።

ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ላይ የተመሠረተ የማጥቃት አወቃቀር ያላቸው አዳማ ከተማዎች በተለይም በዚህ ጨዋታ በንፅፅር ፈጣን ያልሆኑት የሰበታ ተከላካዮችን ይፈትናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአዳማ ከተማዎች በኩል በተለይ ከሰሞኑ አስደናቂ ብቃት ላይ የሚገኘው መናፍ ዐወል፣ ምኞት ደበበ እና ቴዎድሮስ በቀለ የተመሰረተው የሦስት ተከላካዮች ጥምረት የአዳማ ጠንካራ ጎን ሲሆን ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ እንደማድረጉ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የተከተለውን አሰላለፍ በድጋሚ ይዞ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

አዳማ በመከላከል አደረጃጀት ላይ ያለውን ጥንካሬ በማጥቃት ወቅት ለመድገም ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቀው በሁለቱ ጨዋታዎች አሳይቷል። ቡድኑ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ለመፍጠርን ከመቸገር በተጨማሪ ያገኘውን እድል በአግባቡ መጠቀም ላይ ምን ያህል እንደተዘጋጁ የነገው ጨዋታ ምላሽ የሚኖረው ይሆናል።

በአዳማ በኩል በጉዳት የሰነበተው ብሩክ ቃልቦሬ ልምምድ ሲጀምር ባለፈው ጨዋታ ያልተሰለፈው ከነዓን ማርክነህም በተመሳሳይ ወደ ልምምድ ተመልሷል። በዛሬ ልምምድ ላይ ያልነበሩት ቡልቻ ሹራ እና ሚካኤል ጆርጅ ደግሞ የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ነው።

የእርስ በርስ ግነኙነት

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ከስምንት ዓመታት በኋላ የመጀመርያ ጨዋታ ሲያከናውኑ እስካሁን ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ሦስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት አለው። ሰበታ ከተማ አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

– በስድስቱ ጨዋታዎች ስድስት ጎሎች ሲቆጠሩ አዳማ 4፣ ሰበታ 2 አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል አጃይ

ጌቱ ኃይለማርያም – አዲስ ተስፋዬ – ሳቪዮ ካቡጎ – ኃ/ሚካኤል አደፍርስ

ደሳለኝ ደባሽ – ታደለ መንገሻ – ዳዊት እስጢፋኖስ

ናትናኤል ጋንቹላ – ፍፁም ገ/ማርያም – ባኑ ዲያዋራ

አዳማ ከተማ (3-5-2)

ጃኮ ፔንዜ

ምኞት ደበበ – መናፍ ዐወል – ቴዎድሮስ በቀለ

ፉአድ ፈረጃ – አዲስ ህንፃ – አማኑኤል ጎበና – ኢስሜኤል ሳንጋሬ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሆቴሳ – ኃይሌ እሸቱ


© ሶከር ኢትዮጵያ