በ3ኛው ሳምንት ሌላኛው መርሐ ግብር በሀዋሳ ሰውሰራሽ ሜዳ ሀዋሳ ከተማ ባህር ዳር ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታን በቀጣዩ ዳሰሳ ተመልክተነዋል።
ከመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት አራት አራት ነጥብ ይዘው መልካም ጅማሮን በማድረግ ገና በማለዳው በሊጉ ሰንጠረዥ ከአናት በሚገኙ ሁለት ቡድኖች መካከል የሚደረገው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለሜዳዎቹ ሀዋሳ ከተማዎች በሁለቱም የሊግ ጨዋታዎችና በአዳማ ከተማ ዋንጫ ላይ በነበራቸው ቆይታ ቡድኑ ለመከላከል አደረጃጀት ከፍተኛ አፅንኦት እንደሚሰጥ ለመመልከት ተችሏል። ባሳለፍነው ሳምንት ከሆሳዕና ነጥብ ይዞ ሲመለስ በአመዛኙ ከተወሰኑ የጨዋታ ቅፅበቶች ውጪ በቁጥር በርከት ብለው ለራሳቸው ግብ ቀርበው ሲከላከሉ ተስተውሏል።
ቡድኑ ጨዋታውን በሜዳው እንደማከናወኑ ማሸነፍን ኢላማ ያደረገ ቀጥተኛ የማጥቃት አቀራረብ እንደሚኖረው ሲጠበቅ ወጣቶቹ መስፍን ታፈሰ እና እስራኤል እሸቱን በማጣመር ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ይገመታል።
በሀዋሳ በኩል አስጨናቂ ሉቃስ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ እና አላዛር መርኔ ባለፈው ዓመት በጥሎ ማለፉ እና ፕሪምየር ሊጉ በተመለከቱት ቀይ ካርድ፤ ተከላካዩ መሳይ ጳውሎስ ደግሞ በጉዳት ለጨዋታው አይደርሱም።
በአዲስ መልኩ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እየተገነባ የሚገኘው ባህርዳር ከተማ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ አደጋ ለመፍጠር ጥረት የሚያደርግ ቡድን ነው። በቡድኑ በኩል መልካሙ ዜና በመቐለው ጨዋታ ቡድኑ ከተለያዩ ክፍሎች ግብን ማስቆጠር የሚችሉ ተጫዋቾችን መያዙ እና የቆሙ/ተሻጋሪ ኳሶች አጠቃቀሙ መሻሻሉ ዐምና እንድክመት የሚቀርብበትን ግብ የማስቆጠር ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የነገው ጨዋታ ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ ቀጥተኛ ማጥቃትን በሚመርጡ ቡድኖች እንደመካሄዱ የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ትልቅ ልዩነት እንደሚፈጥሩ ይገመታል። የሀዋሳ አጥቂዎች ከባህር ዳር ተከላካዮች እንዲሁም በሁለቱም በኩል የሚገኙ የመስመር ተጫዋቾች የሚያደርጉት የአንድ ለአንድ ግንኙነት የጨዋታንው ውጤት የመወሰን ኃይል ይኖረዋል።
ለነገው ጨዋታ በጣናው ሞገድ በኩል በመቐለው ጨዋታ የተጎዳው ዜናው ፈረደ ከቡድኑ ጋር ወደ ሀዋሳ ያልተጓዘ ሲሆን ቀሪዎቹ ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል።
እርስ በርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱንም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት (1-1 እና 0-0) አጠናቀዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)
ቤሌንጋ ኢኖህ
ዳንኤል ደርቤ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላውንቴ – ኦሊቨር ኩዋሜ
አለልኝ አዘነ – ተስፋዬ መላኩ – ሄኖክ ድልቢ
ብርሃኑ በቀለ – መስፍን ታፈሰ – እስራኤል እሸቱ
ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)
ሀሪሰን ሄሱ
ሳላምላክ ተገኝ – አዳማ ሲሶኮ – አቤል ውዱ – ሳሙኤል ተስፋዬ
ፍ/ሚካኤል ዓለሙ – ሳምሶን ጥላሁን – ፍፁም ዓለሙ
ፍቃዱ ወርቁ – ማማዱ ሲዲቤ – ወሰኑ ዓሊ
© ሶከር ኢትዮጵያ