ሎዛ አበራ በአዲሱ ክለቧ የመጀመሪያ ዋንጫ አሳክታለች

አስደናቂ ሳምንትን እያሳለፈች በምትገኘው ሎዛ አበራ ሐት-ትሪክ ታግዘው ቢርኪርካራዎች የማልታን ቢኦቪ የሴቶች ሱፐር ካፕ ዋንጫን ማንሳት ችለዋል። 

ከሰሞኑ እጅግ አስደናቂ ጊዜን እያሳለፈች የምትገኘው ሎዛ ዛሬ ምሽት በማልታ ብሔራዊ ስታዲየም ክለቧ ቢርኪርካራ ከምጋር ዩናይትድ ጋር በማልታ ቢኦቪ የሴቶች ሱፐር ካፕ ባገናኘው ጨዋታ ክለቧ በሎዛ አበራ ሐት-ትሪክ አን ማሪ ሳኢድና ራይና ጉዊስቲ ግቦች ታግዘው 5-0 የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ዋንጫ ማንሳት ችለዋል።

ጨዋታው ከወትሮው በተለየ በርከት ያለ ተመልካች የተመለከተው ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ከፍፃሜው ጨዋታ በፊት በማልታ ወንዶች ፕሪምየር ሊግ ቢርኪርካራ ከሲርና ያደረጉትን ጨዋታ ለመልከት ወደ ስታዲየም የገቡ ደጋፊዎች እግረ መንገዳቸውን የሴት ቡድናቸውን አበረታተዋል።

ከቀናት በፊት በሊጉ ክለቧ ሄበርኒያንስን 17 ለ 0 ሲረታ ሰባት ግቦችን ማስቆጠር የቻለችውና በ17 ግቦችን የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሰንጠረዥ በመምራት ላይ የምትገው ሎዛ በዚህ ሳምንት ብቻ ለክለቧ 10 ግቦችን በማስቆጠር ማነጋገሯን ቀጥላለች።


© ሶከር ኢትዮጵያ