ነገ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል የጦና ንቦች ፈረሰኞቹን በሜዳቸው የሚያስተናግዱበት ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ከሁለቱም የሊግ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡናን አሸንፈው በወልዋሎ በጠባብ ውጤት ተሸንፈው በሁለት ጨዋታ ሶስት ነጥብ ያሳኩት ወላይታ ድቻዎች በሜዳቸው ያላቸውን ጥሩ ክብረ ወሰን ለማስቀጠል እና በተከታታይ ጨዋታ ነጥብ ላለመጣል ወደ ነገው ጨዋታ ይገባሉ። ባለፈው ሳምንት ወሳኝ አጥቂያቸው ባየ ገዛኸኝ በጉዳት በማጣታቸው የሚያጠቁበት መንገድ ላይ ለውጥ ያደረጉት የጦና ንቦች አጥቂው ለጨዋታ ዝግጁ መሆኑን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት የታየባቸው የግብ ማግባት ችግር ይፈታላቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ የተስፋዬ አለባቸው ሙሉ በሙሉ ከጉዳት ማገገምም ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው።
ባለፈው ሳምንት ከወልዋሎ ጋር በነበረው ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ያልተቸገሩት ወላይታ ድቻዎች በነገው ጨዋታ አዲስ ከተዋቀረው የፈረሰኞቹ የአማካይ ጥምረት ቀላል ፈተና እንደማይገጥማቸው እሙን ነው። ከዚ በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች በተስፋዬ አለባቸው በቂ ሽፋን እየተሰጠው ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያደረገው የቡድኑ የተከላካይ ጥምረት በነገው ጨዋታ ፈጣኖቹን የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂዎች እንቅስቃሴ የመግታት ትልቅ ሃላፊነት ይዞ ወደ ሜዳ ይገባል።
ቡድኑ በነገው ጨዋታ ጉዳት ላይ ያለው በረከት ወልዴ እና ቅጣቱን ያልጨረሰው ቸርነት ጉግሳ አይጠቀምም በአንፃሩ ከጉዳት የተመለሰው ባየ ገዛኸኝ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፈው ሳምንት ሰበታ ከተማን አሸንፈው የዓመቱ የመጀመርያ። ድላቸው ያስመዘገቡት ፈረሰኞቹ በዚ ጨዋታ ሳልሃዲን ሰዒድን ጨምሮ በርካታ ተጫዋቾቻቸው በጉዳት ቢያጡም ቀላል ግምት አይሰጣቸውም።
ቡድኑ ለወትሮው ከሚጠቀምበት በመስመሮች በኩል የሚደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ተወስኖ የነበረውን አማራጩን ዘንድሮ በትንሹም ቢሆን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ በሊጉ ያደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ምስክሮች ናቸው። በተለይም ከመቐለ ቡድኑን የተቀላቀለው ሀይደር ሸረፋ ይበልጥ ቡድኑን እየተላመደ ሲሄድ ለቡድኑ መሀል ለመሀል ጥቃት የመሰንዘርያ አማራጭ ሊፈጥር እንደሚችል የሰበታው ጨዋታ ማሳያ መሆን ይችላል ተጫዋቹ በተለይ ከሜዳ ተቀይሮ እስኪወጣ ድረስ ከሳልሀዲን ሰኢድ ጋር የፈጠረው መናበብ የቡድኑ ደጋፊዎች በቀጣይ ከሁለቱ ጥምረት ብዙ እንዲጠብቁ የሚያደርግ ነው።
ምንም እንኳን በነገው ጨዋታ ቡድኑ የሳልሀዲን ሰኢድን ግልጋሎት ማግኘት አለመቻሉ ትልቅ ተግዳሮት ቢሆንም ፈጣኑ አቤል ያለው ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። በመከላከሉ ረገድም ቢሆን ቡድኑ አስቻለው ታመነ ቢያጣም እንኳን ኢድዊን ፍሪምፖንግ በግሉ የተጋጣሚን ጥቃቶች በመመከት በኩል ስኬታማ ጊዜያትን በማሳለፍ ቡድኑን ጠንካራ የመከላከል አቅም አላብሶታል።
በነገው ጨዋታ ሳልሀዲን ሰኢድ፣ ሳልሀዲን ባርጌቾ፣ ፓትሪክ ማታሲ፣ ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ለዓለም ብርሃኑ እና አሜ መሐመድ በጉዳት ምክንያት ቡድናቸው አያገለግሉም።
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ ወላይታ ድቻ (አንድ ፎርፌ ጨምሮ) አራቱን ድል አድርጓል። ቀሪዎቹን ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
– በአስራ ሁለቱ ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ 17 ጎሎች ሲያስቆጥሩ የጦና ንቦቹ ደግሞ (ሦስት የፎርፌ ጎሎች ጨምሮ) 11 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)
መክብብ ደገፉ
ያሬድ ዳዊት – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – ፀጋዬ አበራ
ተስፋዬ አለባቸው
ዘላለም ኢያሱ – እድሪስ ሰዒድ – ነጋሽ ታደሰ – ፀጋዬ ብርሀኑ
ባዬ ገዛኸኝ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)
ባህሩ ነጋሽ
አብዱልከሪም መሐመድ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ምንተስኖት አዳነ – ሄኖክ አዱኛ
ያብስራ ተስፋዬ – ሙሉዓለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ
አቡበከር ሳኒ – ዛቦ ቴጉይ – አቤል ያለው
© ሶከር ኢትዮጵያ