በ3ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ሰበታ ከተማ ከ አዳማ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሰበታዎች በሳምንቱ አጋማሽ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈው ቡድን ውስጥ ተከላካዩ ሳቪዮ ካቩጎ፣ ሳሙኤል ታዬ እና ናትናኤል ጋንቹላን አሳርፈው በምትካቸው ከቅጣት የተመለሰው አዲስ ተስፋዬ፣ አስቻለው ግርማ እና ባኑ ዲያዋራን ተጠቅመዋል። አዳማ ከተማዎች ደግሞ መናፍ ዐወል፣ ፉአድ ፈረጃ፣ ሚካኤል ጆርጅ እና ኢስማኤል ሳንጋሬን አሳርፈው ሱሌይማን ሰሚድ፣ ሱሌይማን መሐመድ፣ ከነዓን ማርክነህ እና ቡልቻ ቡራን በምትካቸው አስገብተዋል።
በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች አዳማ ከተማዎች ሰበታን ኳስን እንዳይመሰርቱ በከነዓን ማርክነህና ዳዋ ሆቴሳ ጫና ውስጥ በመክተት ረጃጅም ኳሶችን እንዲጥሉ ማድረግ ችለዋል ነበር። በ4ኛው ደቂቃ ባኑ ዲያዋራ ከግራ መስመር ያሻማውና ፍፁም በግንባሩ ሞክሯት ወደ ውጭ የወጣችበት እንዲሁም በ8ኛው ደቂቃ ዳዋ በተመሳሳይ ከግራ መስመር አሻምቶለት ቡልቻ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጭ የወጡባቸው ኳሶች በመጀመሪያ ደቂቃዎች የተደረጉ ሙከራዎች ነበሩ።
በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ለወትሮው ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት ጥረት የሚያደርጉት አዳማዎችን እንቅስቃሴ የሰበታው ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጄይ ከግቡ በፍጥነት በመውጣት ሲያመክን ተስተውሏል።
በሒደት እየቀዘቀዘ በመጣው ጨዋታ ሰበታዎች የተሻለ ኳስን ለመቆጣጠር እንዲሁም በአዳማ ከተማዎች በኩል በመልሶ ማጥቃት የመጫወት አዝማሚያዎችን ተመልክተናል። በ35ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ የግብ ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተመልክቶ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ዳንኤል አጃይ በሚገርም ብቃት ሲያወጣበት በተቃራኒው በሰበታዎች በኩል በሰከንዶች ልዩነት ባኑ ዲያዋራ ከግራ መስመር አጥብቦ የመታውን ኳስ ጃኮ ሊያድንበት ችሏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች አስቻለው ግርማ ከሳጥን ጠርዝ ተጫዋቾችን ቀንሶ ወደ ግብ የላካትና ፔንዜ ያዳነበት ኳስ ሁለቱ ክለቦች ለእረፍት 0-0 ከመውጣታቸው በፊት የተደረገች ሙከራ ነበረች።
በሁለተኛው አጋማሽ ሰበታዎች ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በአንፃሩ አዳማዎች በመልሶ ማጥቃት አስፈሪነታቸው በዚህኛው አጋማሽ ጨምሮ ተስተውሏል።
ባኑ ዲያዋራ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ድንቅ የማግባት አጋጣሚ ቢያመክንም ከደቂቃዎች በኃላ ዳዊት ከማእየዕዘን ምት በአጭሩ የተቀበለውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ የላከዝና ጃኮ ፔንዜ ያመከነበት ኳስ ተጠቃሾች ናቸው። 69ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት በረከት ደስታ ከሰበታ ከተማ ተጫዋቾች ጋር ታግሎ ያቀበለውን ኳስ ቡልቻ ሹራ ወደ ግብ የላካትና የግቡን አግዳሚ ለትሞ የተመለሰው ኳስ ደግሞ የጨዋታው አስቆራጭ ሙከራ ነበር።
በ70ኛው ደቂቃ ከነዓን ማርክነህ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረውን እንዲሁም በ74ኛው ደቂቃ ደግሞ በሰበታዎች በኩል ጌቱ ከቀኝ መስመር ያሻማውንና በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው አሊ በግንባሩ የሞከራቸው ኳሶች ሌሎች ተጠቃሽ ሙከራዎች ናቸው።
ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሰበታ ከተማዎች የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ነጥብ ማስመዝገብ ችለዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ