በ3ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሶዶ ላይ በወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል ጨዋታ ተደርጎ ያለግብ ከተጠናቀቀ በኃላ የሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ እንደሚከተለው ሰጥተዋል፡፡
“በፍፁም የዛሬው አጨዋወት ቡድኔን አይገልጽም” ገብረክርስቶስ ቢራራ – ወላይታ ድቻ
ስለ ጨዋታው ደካማ እንቅስቃሴ…
“ሁኔታዎች ናቸው እንዲህ እንድንጫወት ያስገደዱን፤ እንዲህ መጫወት ግን አንፈልግም። የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ጥቅጥቅ ብሎ መሀል ሜዳው ላይ ነው ያለው። ስለዚህ ያን መጫወት ስላልቻሉና ከተከላካዮቹ ጀርባ ክፍት ቦታ ስለነበር ያን እንጠቀማለን በሚል ነው። አንተ ያልከው እቅድህ አንዳንድ ጊዜ ተፎካካሪ ቡድን በሚያመጣው ተቃራኒ አጨዋወት ምክንያት ጨዋታዎች ይበላሽብሀል። እኛ ላይም የሆነው ይሄ ነው፡፡
ቡድኑ ካለፉት ጨዋታዎች ወርዶ መታየቱ
“በፍፁም የዛሬው አጨዋወት ቡድኔን አይገልጽም። ምክንያቱም አይታችሁ ከሆነ የተወሰነ ኳሶችን እንጀምር እና ስንሄድ ይቆራረጣሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የጊዮርጊስ ቡድን ጥቅጥቅ ብሎ መጫወት ነው። እነሱ የፈለጉት ጨዋታውን ገለው በዚህ አይነት መሄድ ስለነበረ የፈለጉትን ነገር አሳክተዋል፣.፤ ለኛ ጥሩ ባይሆንም..”
“በዚህ ሜዳ ላይ ማንም ሦስት ነጥብ መውሰድ አይችልም” ሰርዳን ዝቪጅሆቭ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስለ ጨዋታው
” አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ክለቦች እየተሻሻሉ መጥተዋል። በዚህም የተነሳ እያንዳንዱን ጨዋታ ማሸነፍ አይቻልም። አንድ አሸንፈናል፤ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተን ወጥተናል። ግን በተቻለን አቅም እያንዳንዱን ጨዋታ ለማሸነፍ እንጥራለን።
” በዛሬው ጨዋታ ታክቲካል ቡድን ነበርን፤ ምክንያቱም በዚህ ሜዳ ላይ ማንም ሶስት ነጥብ መውሰድ አይችልም፡፡ ህዝቡም ደግሞ በዚህ ሜዳ በሚደረግ ጨዋታ በፍፁም መደሰት አይችልም፡፡ በአጠቃላይ ይህ ሜዳ ፈርሷል ብለው ይቀለኛል። ቡድኔ መከላከል ላይ ጥሩ ነው ፤ ማጥቃቱ ላይ አሁንም ክፍተት አለብን። ይህን ለማስተካከል በቀጣይ እንሰራለን፡፡ ”
© ሶከር ኢትዮጵያ