ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ የዓመቱን የመጀመርያ ድል አስመዘገበ

ድሬዳዋ ላይ በሦስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለት ተከታታይ ሽንፈትን ከሜዳው ውጪ አስተናግዶ የተመለሰው ድሬዳዋ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን በሪችሞንድ አዶንጎ ግብ 1-0 በማሸነፍ እፎይታን አግኝቷል፡፡

ከድሬዳዋ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ቀደም ብሎ 8:00 ላይ የቀድሞ የድሬዳዋ ኮተን እና የምድር ባቡር ተጫዋቾች ለሰላም እንነሳ በሚል የወዳጅነት ጨዋታን ያደረጉ ሲሆን በጨዋታውም ለምድር ባቡር ተሰልፎ የገባው አንጋፋው አጥቂ ዮርዳኖስ ዓባይ አንድ ግብ በማስቆጠር የቀድሞው የድሬዳዋ ባቡር ተጫዋቾችን አሸናፊ አድርጓል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል ባለፈው ሳምንት በፋሲል 5-0 ከተሸነፈው ስብስብ በፍሬዘር ካሣ፣ ፍሬድ ሙሸንዲ፣ ያሬድ ሀሰን፣ ሙህዲን ሙሳ ምትክ ዘሪሁን አንሼቦ፣ አማረ በቀለ፣ ሳሙኤል ዘሪሁን እና ያሬድ ታደሰ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ሲካተቱ ሀዲያ ሆሳዕናም በተመሳሳይ ከሀዋሳ አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በርካታ ለውጥ በማድረግ በሱራፌል ዳንኤል፣ አብዱልሰመድ አሊ፣ ሙሳ ካማራ፣ ቢስማርክ ኦፖንግ ምትክ ፍራኦል መንግሥቱ በኃይሉ ተሻገር፣ ኢዩኤል ሳሙኤል እና መሐመድ ናስርን አሰልፏል።

9:00 ሲል በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያውን 15 ደቂቃ በኳስ ቁጥጥሩ ድሬዳዋ ከተማ ተሽሎ ሲታይ በአመዛኙ ግን ተመጣጣኝ ይዘት ነበረው። በዚህም ገና በጊዜ ያሬድ ታደሰ እንዲሁም አማካዩ ኤልያስ ማሞ በፍጥነት ወደ ሀድያ የግብ ክልል ደርሰው የሞከሯቸው አጋጣሚዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በ28ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የሀዲያ ሆሳዕናው እዩኤል ሳሙኤል ወደ ጎል ተቃርቦ የድሬዳዋ ከተማው ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን ያዳነበት የዕንግዳዎቹ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

ድሬዳዋ ከተማዎች ያለፉት ሁለት ጨዋታዎችን በሽንፈት እንደመምጣታቸው እልህ የተቀላቀለበትን ድንቅ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ 35ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ታደሰ ከርቀት የመታት ኳስ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ነክታ የወጣች ሲሆን 43ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያ ሆሳዕናው እዩኤል ሳሙኤል ካደረገው ተጨማሪ ሙከራ ሁለት ደቂቃዎች በኋላ በኃይሉ ተሻገር ወደ ጎል የሞከራት ኳስ የድሬዳዋው ከተማ ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን እንደምንም አውጥቷት ግብ ከመሆን ድናለች፡፡

2ኛው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች በመጠኑ ተዳክመው ሲገቡ ሀድያ ሆሳዕናዎች ግን በማጥቃቱ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ማጥቃት ላይ እጅጉን የተሻሉ የነበሩት ሆሳዕናዎች በክፍት የጨዋታ ሂደት ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረው የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን አቅሙን በተደጋጋሚ በመጠቀም ሲያመክናቸው ታይቷል፡፡ 53ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያ ሆሳዕናው ፍራኦል መንግስቱ በግራ ክንፍ በኩል ሞክሯት የወጣችው ኳስም አስቆጪ አጋጣሚ ነበረች፡፡

በተደጋጋሚ የአሰልጣኝ ስምዖን አባይን ድሬዳዋ ከተማ የተከላካይ ክፍልን በማስከፈት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ የታዩት ሀድያ ሆሳዕናዎች 63ኛው ደቂቃ ላይ በእዩኤል ሳሙኤል ከርቀት አክርሮ መቶ የሞከራት በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ለተጫወቱት እንግዳዎቹ ለግብ መቃረባቸውን ያሳየች መልካም ዕድል ነበረች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተዳክመው የታዩት ድሬዳዋ ከተማዎች በ77ኛው ደቂቃ ሦስት ነጥብ ያገኙባትን ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ከሆሳዕና የግብ ክልል ጠርዝ የተገኘውን ቅጣት ምት በረጅሙ ኤልያስ ማሞ ሲያሻማ በቀኝ በኩል ተከላካዩ ዘሪሁን አንሼቦ ጋር ደርሳ ዘሪሁን መሬት ለመሬት ወደ ግብ ሲመታው ታሪክ ጌትነት ለመያዝ ጥረት ቢያደርግም ከእጁ በማምለጡ ፊት ለፊቱ የነበረው አዲሱ የድሬዳዋ ፈራሚ ሬችሞንድ አዶንጎ በቀላሉ አስቆጥሮ ብርቱካናማዎቹን መሪ አድርጓል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኃላ ማፈግፈግን ምርጫቸው ያደረጉት ድሬዎች በሀድያ የማጥቃት ብልጫ ቢወሰድባቸውም በጥብቅ በመከላከል መሪነታቸውን አስጠብቀው ወጥተዋል።

ድሉ ለድሬዳዋ ከተማ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና ከሦስቱ ጨዋታዎች ድል ማስመዝገብ አልቻለም።


© ሶከር ኢትዮጵያ