የአሰልጣኞች አስተያየት| ወልቂጤ ከተማ 1–0 ፋሲል ከነማ

በ3ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም ወልቂጤ ከተማ ፋሲል ከነማን 1-0 ካሸነፈ በኋላ የአሰልጣኞች አስተያየት ይህን ይመስላል።

“ተጫዋቾቼ ከሜዳችን ውጭ በመጫወታችን ያጣነውን ጥቅም ተቋቁመው አራት ነጥብ ማስመዝገብ ችለናል” የወልቂጤ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው

ሜዳ ላይ እንቅስቀቃሴ

በጣም ልምድ ያካበተ፣ ጠንካራ ስብስብ ያለው እና በጠንካራ አሰልጣኝ የሚመራ ቡድን ነው። ወልቂጤ ከታች የመጣ እና በወጣቶች እንደተገነባ ቡድን ነው። ተጫዋቾቼ ዛሬ በሜዳ ላይ ለማሸነፍ የከፈሉት መስዋትነት ከፍ ያለ ነበር። እስካሁን በመጣንባቸው ሁለት ጨዋታዎች የሚችሉትን ሁሉ ለመስጠት ሜዳ ላይ ጥረት አድርገዋል። የእግርኳስ ነገር ሆኖ ባይሳካልንም። ዛሬ ግን ጥረታቸው ተሳክቶ ጎል አግብተን ማሸነፍ ችለናል። ሁለተኛው አጋማሽ ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችል ዕድሎች አግኝተን አልተጠቀምንም። በቀጣይ ችግሮቻችንን እየቀረፍን የተሻለ ነገር ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን። በአጠቃላይ ግን ጨዋታው ፈጣን ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት እልህ አስጨራሽ በጣም የተደሰትኩበት ነበር።

ከሜዳ ውጭ መጫወት ተፅዕኖ

ይህ ግልፅ ነው። በየትኛውም ስፖርት ከሜዳህ ውጭ ስትጫወት ብዙ ጉዳቶች አሉት። በሜዳህ ላይ ስትጫወት የምታገኛቸውን ጥቅሞች ሁሉ ታጣለህ። ልጆቻችን በሜዳቸው ሲጫወቱ የሚያገኙትን በራስ መተማመን ያጣሉ፣ ከሜዳ ውጭ አኳያ ብናነሳ እንኳ የወልቂጤ ከተማን ማህበረሰብ ተጠቃሚነቱን ያጣል፣ እግርኳሱ በማህበረሰቡ እንዳይነቃቃ ያደርጋል። እነዚህ በሰፊው ያጣናቸው ትልልቅ ዋጋ እያስከፈሉን ነገሮች ናቸው። ከሜዳችን ውጭ በመጫወታችን ያጣነውን ጥቅም ተቋቁመው ልጆቼ ሦስት ጨዋታ ከሜዳ ውጭ ተጫውተው በከፍተኛ ጥረት አራት ነጥብ ማስመዝገብ ችለናል።

በቀጣይ ምን እንጠብቅ

ገና እየተሰራ ያለ አዲስ ቡድን ነው። እግርኳስ ደግሞ ሂደት ነው፤ ጊዜ ይፈልጋል። የዛሬው ድላችን የምንታበይበት ወይም ስራችንን ጨርሰናል የምንለበት አይደለም። በማሸነፍ ውስጥ በጣም ብዙ ክፍተቶች አይተናል። ልጆቼ ለስራ ያላቸው ተነሳሽነት፣ የማሸነፍ ፍላጎታቸው ከፍ ያለ በመሆኑ እና ወጣት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በቀጣይ ብዙ ስራ ከፊታችን ይጠብቀናል። ከሰራን በጠነከርን ቁጥር በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነን ለመቅረብ በቀጣይ እንሰራለን።

“በማሸነፍም በመሸነፍም የምትማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤ በቀጣይ አስተካክለን እንመጣለን”። የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ

ከሜዳው አለመመቸት አኳያ የምንፈልገውን ነገር ማድረግ ቢከብደንም የተገኙትን አጋጣሚዎች አለመጠቀም ዋጋ አስከፍሎናል። የእኛ መዘናጋት ኳሱ ከጨዋታ ውጭ ነው አይደለም በማለት ተከላካይ ላይ ክፍተት ነበር። ለማንኛውም ከእረፍት መልስ ተጭነን ለመጫወት ጥረት አድርገን አልተሳካም። እነርሱ የመጀመርያው አጋማሽ የጎል አጋጣሚ አግኝተው ተጠቅመዋል። እኛ ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ ብዙ ዕድሎችን ፈጥረን ሊሳካ አልቻለም። በጥሩ ብቃት እያገለገለን የመጣው ሽመክት ጉግሳ ገና በጨዋታው ጅማሬ መጎዳት ተፅእኖ አድርጎብናል። በአጠቃላይ ለእኛ ትምህርት የሚሆን አይደልም። በዚህ ሜዳ ላይ ውድድር ማድረግ በራሱ ከባድ ነው። ለቀጣይ ጨዋታዎቻችን ትኩረት እናደርጋለን። ከዝግጅት ጀምሮ በውድድር ለእኛ የመጀመርያ ሽንፈታችን ነው። በማሸነፍም በመሸነፍም የምትማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤ በቀጣይ አስተካክለን እንመጣለን።

የበዛብህ ተጠባባቂ መሆን ለጥንቃቄ ነው ?

በዚህ ምቹ ባልሆነ ሜዳ ላይ ስትጫወት ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ለዛም ነው በሁለት የተከላካይ አማካይ ለመጫወት የሞከርነው። በአሁኑ ወቅት ሀብታሙ ጥሩ እየመጣ ይገኛል። ከሜዳ ውጪ የምታደርጋቸው ውድድሮችን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ይሄን ለማድረግ ነው ያሰብነው። የተጫዋች አጠቃቀማችን ብዙ ችግር አልፈጠረብንም። ጥቃቅን ነገሮችን ማስተካከል ብቻ ይጠበቅብናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ