ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ባህር ዳርን በማሸነፍ በጥሩ አጀማመሩ ቀጥሏል

በአማኑኤል አቃናው

በማራኪ እንቅስቃሴ እና በጎል ሙከራ የታጀበው የሀዋሳ ከተማ እና የባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ባለፈው ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ አዲስዓለም ተስፋዬ እና ሄኖክ ድልቢ አርፈው ዘላለም ኢሳይያስ ሄኖክ አየለ ወደ አሰላለፍ ሲካተቱ በባህር ዳር በኩል መቐለን ሲያሸንፉ ጉዳት ባጋጠመው ዜናው ፈረደ ምትክ ግርማ ዲሳሳ ጨዋታውን ጀምሯል።

በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ከቀኑ 09፡00 ላይ በሊጉ የሦስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር የተገናኙት የሀዋሳ ከተማ እና የባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር የተጀመረ ነበር። በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ ሀዋሳዎች በተደጋጋሚ ወደ ጎል ሲደርሱ ታይተዋል። በዚህም በሄኖክ አየለ፣ እስራኤል እሸቱ እና አለልኝ አዘነ ሙከራዎች ሀሪሰን ሄሱን ለመፈተን ሞክረዋል። በተለይም ቡድኑ ከዳንኤል ደርቤ የሚነሱ ኳሶችን ለማጥቃት ሲጠቀምባቸው ተስተውሏል። በአንፃሩ እንግዶቹ ባህር ዳሮች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለመያዝ በመሞከር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ ለለድረስ ጥረት አድርገዋል።

24ኛው ደቂቃ ካይ የሀዋሳው አጥቂ እስራኤል እሸቱ ጉዳት ገጥሞት ለመውጣት ሲገደድ እሱን ተክቶ የገባው ብሩክ በየነ ከዘላለም ኢሳይያስ የተቀበለውን ኳስ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ሀሪሰን አድኖበታል። ጨዋታው ቡድኖቹ መሀል ሜዳ ላይ ብልጫ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ማራኪ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን በመስፍን ታፈሰ እና ዳንኤል ደርቤ በመስመር በኩል ጥቃት ሲሰነዝሩ የነበሩት ሀዋሳዎች 32ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አግኝተዋል። ግቧን ከመስመር ያመቻቸው መስፍን ታፈሰ ሲሆን አስቆጣሪው ደግሞ ብሩክ በየነ ሆኗል። ባህር ዳሮች ግብ ካስተናገዱ በኋላ በወሰኑ አሊ እና ግርማ ዲሳሳ አማካይነት የአቻነት ግብ ለማግኘት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የሀዋሳዎች የመስመር ጥቃት ተበራክቶ የቀጠለ ሲሆን ሣላምላክ ተገኝን በሚኪያስ ግርማ የለወጡት ባህር ዳሮችም በፍፁም አለሙ ፣ ወሰኑ አሊ እና ማማዱ ሲዲቤ አማካይነት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። ሆኖም ጨዋታውን ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ሀዋሳዎች በመልሶ ማጥቃት በብርሀኑ በቀለ ፣ ብሩክ በየነ እና ዳንኤል ደርቤ አማካይነት ሙከራዎችን በማድረግ ምላሽ መስጠታቸው አልቀረም ።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ሀዋሳዎች ሄኖክ አየለን በየተሻ ግዛው ባህር ዳሮች ደግሞ ወሰኑ አሉን በስታየሁ መንግስቱ ፤ ሳምሶን ጥላሁንን በደረጄ መንግስቱ በቀየር ለውጦችን አድርገው ይበልጥ ጫና ለመፍጠር ጥረታቸውን ቀጥለዋል።

የቡድኖቹ ፉክክር እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቀጥሎም ሀዋሳዎች በብሩክ በየነ እና ብርሀኑ በቀለ ሁለተኛ ግብ ለማካል ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ በመጨረሻ ደቂቃ ከቅጣት ምት ግብ ለማግኘት ተቃርበው የነበሩት ባህር ዳሮችም የአቻነታን ጎል ሳያገኙ ጨዋታው በሀዋሳ 1-0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

በጨዋታው ባህር ዳር ከተማው አማካይ ፍጹም ዓለሙ የማልያ ቁጥር አደናጋሪ ነበር። በተጫዋቾች ዝርዝር ላይ 14 ቁጥር እንደለበሰ የሚገልፀል ሲሆን በሜዳ ላይ ተጫዋቹ ማልያው 6 ቁጥር ቁምጣው ደግሞ 14 ቁጥር ሆኖ ይታያል።


© ሶከር ኢትዮጵያ