የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-0 ባህር ዳር ከተማ

በአማኑኤል አቃናው

ሀዋሳ ላይ በሦስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ በብሩክ በየነ ብቸኛ ግብ 1-0 ባህር ዳርን ከረታ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንዲህ ገልፀዋል፡፡


“በቡድኔ ደስተኛ ነኝ፤ ከዕለት ዕለት መሻሻል ይታይበታል” አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው በተደጋጋሚ ወደ ጎል የቀረብንበት የተሻልን የነበርንበት ነበር። በአንድ ጨዋታ ደግሞ ዋነኛው ወደ ግብ መቅረብ ነው፡፡ አሁንም የማስቆጠር ችግር እንደክለብ አለብን። በርትተን እንሰራለን። በነበረን እንቅስቃሴ ግን ደስተኛ ነኝ፡፡ ግብ ላይ መድረስ ከቻለን ማግባት ላይ ያለንን ክፍተት በቀጣይ ጨዋታዎች እያስተካከልን እንመጣለን፡፡

ስለ እሰራኤል እሸቱ ጉዳት

አሁን እሱን ለመናገር ይከብዳል። ልምድ ያለው ተጫዋች ነው፤ ቢኖር ይጠቅመናል፡፡ እሱን ተክቶ የገባው ብሩክ ከሱ በልምድ ቢያንስም ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል፤ ግብም አስቆጥሯል። በቡድኔ ደስተኛ ነኝ፤ ከዕለት ዕለት መሻሻል ይታይበታል፡፡

“ውጤቱ ይገባቸዋል” ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው

በመጀመሪያ ሀዋሳ ከተማዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፤ ውጤቱ ይገባቸዋል፡፡ ነጥብ ለማግኘት ነበር ወደ ጨዋታው የገባነው። ሆኖም ከነሱ ከመስመር የሚነሱ ኳሶች በፍጥነት ስለሚመጡ መቆጣጠር ተስኖን ነበር፡፡ እናም በመልሶ ማጥቃት በተደጋጋሚ በሁለቱም መስመሮች ይሰነዝሩብን ነበር፡፡ ያ ደግሞ ግብ እንዲቆጠርብን ሆኗል፡፡ ሁለተኛ ኳሶች ላይም ጥሩ አልነበርንም፡፡ እንግዲህ ኳስ ነው፤ ለቀጣይ ጨዋታዎች ተሻሽለን እንቀርባለን ፡፡ በሜዳ ላይ ባየሁት የስፖርታዊ ጨዋነትም ደስተኛ ነበርኩ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ