በማቲያስ ኃይለማርያም እና አምሀ ተስፋዬ
የ2012 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው አዲስ አዳጊው ሶሎዳ ዓድዋ ከሜዳው ውጪ ገላንን 3-0 በማሸነፍ ድንቅ ጅማሮ አድርጓል። ደደቢት ከኤሌክትሪክ ደግሞ 1-1 ተለያይተዋል።
ረፋድ አራት ሰዓት ላይ በትግራይ ስታዲየም የተደረገው የደደቢት እና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። አሰልቺ እና በሙከራዎች ያልታጀበው የመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ግዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል ጥሩ የማጥቃት አጨዋወት ያልታየበት ሆኖ ሲያልፍ ጨዋታውም በበርካታ የዳኝነት ስህተቶች የታጀበ ነበር።
ቢንያም ደበሳይ በሁለት አጋጣሚዎች ባደረጋቸው ሙከራዎች ጥቃታቸው የጀመሩት ሰማያዊዎቹ በአጋማሹ በዲሜጥሮስ ወ/ሥላሴ አማካኝነት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በሙከራዎች ባልታጀበው አጋማሽ ኤሌክትሪኮች ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
ከተጋጣምያቸው አንፃር በተሻለ መልኩ ወደ ግብ የቀረቡት ደደቢቶች በመጀመርያ አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ላይ በከድር ሳልሕ አማካኝነት ጥሩ የግብ ሙከራ ማድርግ ችለዋል። ሆኖም አማካዩ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ የመታት ኳስ ለጥቂት ነበር የወጣችው።
ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር የተሻሉ የማጥቃት አጨዋወቶች የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በርካታ የግብ ዕድሎች ተፈጥረውበታል። በመስመሮች እና በመልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉት ደደቢቶች አፍቅሮት ሰለሞን እና ፉሴይኒ ኑሁ ተቀይሮ ከገባ በኃላ በተሻለ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ደርሰዋል። ከፈጠሯቸው የግብ ዕድሎችም ውስጥም ሃይሉ ገ/የሱስ አሻምቶ ፉሴይኒ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረው እና በጨዋታው ኮከብ ሆኖ የዋለው ዓብዱልሐፊዝ ቶፊቅ ከአፍቅሮት ሰለሞን ጋር ተቀባብሎ ከግብ ጠባቂው ጋር በመገናኘት ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ። በሰባ ሶስተኛው ደቂቃም ዓብዱልበሲጥ ከማል ከከድር ሳልሕ የተሻገረለት ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ሲችል የውድድር ዘመኑ የመጀመርያ ጎል አስቆጣሪ መሆንም ችሏል።
ደደቢቶች ከግቡ በኋላም በከድር ሳልሕ እና ዮሐንስ ፀጋይ አማካኝነት ሙከራ ቢያደርጉም ጥረታቸው አልሰመረም። በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ በመንቀሳቀስ የግብ ዕድሎች የፈጠሩት ኤሌክትሪኮችም በሐብታሙ ረጋሳ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው ተከላካዮች ተደርበው አውጥተውታል። ከዚ ውጭ ዮሐንስ ተስፋዮ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ያመከናት ወርቃማ ዕድልም በኤሌክትሪክ በኩል አስቆጪ ነበረች። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ሰዓት ኤሌክትሪኮች በወ/አማኑኤል ጌቱ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።
በጨዋታው 34ኛ ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪኩ አጥቂ ሳዲቅ ተማም የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል።
ቢሾፍቱ ላይ ሶሎዳ ዓድዋን ያስተናገደው የዐምናው ጠንካራ ተፎካካሪ ገላን 3-0 ተሸንፏል። ተቀዛቅዞ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጅማሮ የጠራ የግብ እድሎችን ባያስመለክትም ቀስ በቀስ እየተሟሟቀ ሄዷል። ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት ጨዋታውን በራሳቸው ቅኝት ለመቃኘት አስበው የተንቀሳቀሱት ባለሜዳዎቹ በ7ኛው ደቂቃ አንተነህ አምሳሉ በግል ጥረቱ ከመስመር እየገፋ ሄዶ በሞከረው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የነበር ቢሆንም ናይጀሪያዊ ግብ ጠባቂ ሰንደይ አድኖባቸዋል። 4-5-1 አሰላለፍ ይዘው ወደ ሜዳ የገቡት አዳዎች ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት በመጣል የገላንን ግብ ክልል መፈተሽ ችለዋል። በ11ኛው ደቂቃ ላይም የገላን ተከላካይ ክፍል በሰራው ስህተት በተገኘ ቅጣት ምት ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ እንድሪያስ ሀፍቶም በግንባሩ በመግጨት ሶሎዳን መሪ የምታደርግ ግብ አስቆጥሯል።
እየተሟሟቀ የቀጠለው ጨዋታው ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ ብርቱ ፉክክር አስተናግዷል። በ32ኛው ደቂቃ የገላን ተከላካዮች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ ጥሩ ኳስ ያገኘው አምበሉ የማነ ገብረስላሴ አክርሮ መቶ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻለም። ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ሰብረው መግባት የተሳናቸው ገላኖች በጅብሪል እና ወንድምአገኝ ሌላ የርቀት ኳስ ግብ ለማስቆጠር ሞክረው ወደ ውጪ ወጥቶባቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪው ሰዓት ዳግም ጥሩ እድል ያገኙት ገላኖች አቻ ሆነው ወደ እረፍት የሚያመሩበትን እድል በኤርምያስ ኃሀይሌ አማካኝነት ፈጥረው የነበር ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ያስመለከተው ሁለተኛው አጋማሽ ሙከራ ለማስተናገድ ደቂቃዎች አልፈጀበትም። በ47ኛው ደቂቃ ተደራጅተው ወደ ሶሎዳዎች የግብ ክልል የደረሱት የዳዊት ታደለ ተጫዋቾች በፌልሞን ገብረፃዲቅ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ በማድረግ የሶሎዳ አዳዋ ግብ ፈትሸዋል። ኳስ ለተጋጣሚ ሰጥተው ጨዋታቸውን ማድረግ የቀጠሉት አደረዋዋች ከየአቅጣጫው ጥቃቶች ሲሰነዘርባቸው ታይቷል። ፌሊሞን ሙከራ ካደረገ ከሁለት ደቂቃ በኋላም በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ሶሎዳ የግብ ክልል ያመሩት ገላኖች በወንድም አገኝ አብሬ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋ የነበር ቢሆንም ሰንደይ አድኖበታል።
ሶሎዳዎች ምንም እንኳን ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ቢከላከሉም ፍጥነት የታከለበት ሽግግር በማድረግ ግብ ማስቆጠራቸውን ቀጥለውበታል። በዚህም በ55ኛው ደቂቃ ገላኖች ትተውት የሄዱትን ሜዳ በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት እንድሪያስ ያሻገረውን ኳስ የግብ ጠባቂው ስህተት ታክሎበት ሙሉዓለም በየነ በነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ኃይሉሽ ፀጋይ አቀብሎት ኃይሉሽ የቡድኑን ሁለተኛ ጎል አስቆጠረሯል።
ጥቃት መሰንዘረቀቸውን የቀጠሉት ባለሜዳዎቹ በ65፣ 67 እና 73ኛው ደቂቃ ከመስመር ባሻሟቸው ኳሶች ጥሩ ጥሩ እድል ቢፈጥሩም ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። በሁለቱም አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየው ሙሉዓለም በ67ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር በቅጣት ምት ከተገኘውን አጋጣሚ ከተከላካዩቹ ማሀል በሙሽለክ በግንባሩ ሶስተኛ ግብ አስቆጥሮ የሶሎዳን አሸናፊነት ማረጋገጥ ችሏል።
በሙሉ ኃይላቸው ወደ ግብ ያመሩት ገላኖች በጅብሪን እና ወንድምአገኝ አብሬ አስቆጪ የግብ እድሉች ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። ጨዋታውም በሶሎዳ ዓድዋ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውድድሩ ነገ በሦስቱ ምድቦች በሚደረጉ 14 ጨዋታዎች ይቀጥላል።
© ሶከር ኢትዮጵያ