ቅድመ ዳሰሳ | መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በነገው ዕለት ከሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የመቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ባለፈው ሳምንት በጣና ሞገዶች ሽንፈት ያስተናገዱት መቐለዎች በተከታታይ ጨዋታ ነጥብ ላለመጣል የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተው ነው ጨዋታውን የሚያካሂዱት። ቡድኑ ከባለፈው የውድድር ዓመት ጋር በብዙ መልኩ የሚመሳሰል አጨዋወት ይዞ ዓመቱን ሲጀምር በጉዳት ምክንያት ወሳኝ የአማካይ ተሰላፊዎቸው በማጣታቸው በተለይም በቡድኑ የፈጠራ አቅም ላይ በርካታ ክፍተቶች ታይቶባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቡድኑ የአማካይ ክፍል ላይ የተጣመሩት ዳንኤል ደምሱ እና ሙልጌታ ወ/ጊዮርጊስ በማጥቃቱ ላይ የተገደበ ሚና በመያዛቸው ቡድኑ ሁነኛ የሳጥን-ሳጥን አማካይ እጦት ታይቶበታል።

በዋነኝነት በረጃጅም ኳሶች እና በተለጠጡ የመስመር አማካዮች የሚያጠቁት መቐለዎች በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ አጨዋወት እና አደራደር ይዘው ይገባሉ ተብሎ ሲጠበቅ በተጋጣሚያቸው አጨዋወት ምክንያት ከሌላው ግዜ በተለየ በተጋጣሚ ሜዳ ‘Press’ አድርገው መጫወታቸው አይቀሬ ነው።

ምዓም አናብስት በዚ ጨዋታ በረጅም ግዜ ጉዳት የሚገኘው አምበሉ ሚካኤል ደስታ እና ዳንኤል ደምሴን በጉዳት ሲያጡ ጉዳት ላይ የነበረው ያሬድ ብርሃኑ ለጨዋታው ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ ቀለል ያለ ልምምድ የጀመረው አማካዩ ዮናስ ገረመው ለጨዋታው አይደርስም።

በአዲስ አአጨዋወት ዓመቱን የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለቱም የሊጉ ጨዋታዎች ያገኙት ነጥብ አንድ ብቻ ቢሆንም ቡድኑ በሂደት ለውጥ እያሳየ መምጣቱ ታይቷል። በቅድመ ውድድር ግዜ እና በሊጉ የመጀመርያ ጨዋታ ላይ በኳስ አመሰራረት ሂደት፣ በግል በተጫዋቾች በሚሰሩ ጥቃቅን ስህተቶች እና ቡድኑ ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርገው ሽግግር ላይ በርካታ ክፍተቶች የታዩባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በማጥቃቱ ሂደት ላይ ጥሩ ማሻሻሎች ማሳየታቸውን ባለፈው ሳምንት ከጅማ አባጅፋር ጋር በነበረው ጨዋታ ታይቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች የተጋጣሚ መልሶ ማጥቃቶች ለመመከት ሲቸገሩ የታዩት ቡናማዎቹ የተለመደው የመቐለ አስፈሪ የመልሶ ማጥቃት ለመመከት የተለየ ዝግጅት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዚ ጨዋታ የታፈሰ ሰለሞን መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።

እርስ በርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች በአጠቃላይ ለአራት ጊዜያት ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ቡና 3፣ መቐለ 2 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)

ፊሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – ላውረንስ ኤድዋርድ – አስናቀ ሞገስ

ሙልጌታ ወ/ጊዮርጊስ – አሚን ነስሩ

ሳሙኤል ሳሊሶ – ያሬድ ከበደ – አማኑኤል ገ/ሚካኤል

ኦኪኪ ኦፎላቢ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተክለማርያም ሻንቆ

አህመድ ረሺድ – ፈቱዲን ጀማል – ወንድሜነህ ደረጄ – አሥራት ቱንጆ

ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን – ዓለምአንተ ካሣ – አማኑኤል ዮሐንስ

አቤል ከበደ – አቡበከር ናስር – እንዳለ ደባልቄ


© ሶከር ኢትዮጵያ