የቀን ሽግሽግ ተደርጎበት ነገ የሚከናወነው የጅማ አባ ጅፋር እና ሲዳማ ቡናን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
ከሁለት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ማሳካት የቻሉት ጅማ አባጅፋሮች ለሦስተኛ ጊዜ ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ቡድኑ ምንም እንኳን ለመከላከል ቅድሚያ ቢሰጥም የሚገኙ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን መጠቀም ላይ ግን ክፍተቶች ይታይበታል። ቁጥር በርከት ብሎ የሚከላከለው ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ወቅት ከአጥቂው ብሩክ ገ/አብና ፈጣኑ ኤርሚያስ ኃይሉ በስተቀር ተጨማሪ ሰዎችን ወደ ፊት ለመላክ ሲደፍር አይስተዋልም። በዚህም የተነሳ ቡድኑ እስካሁን በሊጉ ምንም ግብ ያላስቆጠረም ያልተቆጠረበት ብቸኛው ቡድን ለመሆን ችሏል።
ቡድኑ የሚገጥመው በመልሶ ማጥቃት አደገኛ ከሚባሉት ቡድኖች አንዱ ከሆነውና ከሊጉ ምርጥ የአጥቂ ጥምረቶች መካከል የሆነው ሲዳማ ቡናን እንደመሆኑ በዚሁ ጨዋታ ላይ ፈጣን የሆኑት የሲዳማ ቡና የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎችን ለማቆም ይበልጥ ጥንቃቄን ጨምሮ ይመጣል ተብሎ ይገመታል።
በጅማ በከል የመስመር ተጫዋቹ ጀሚል ያዕቆብ እና አጥቂው ብዙዓየሁ እንደሻው በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን ከሰሞኑ ከስራ ፈቃድ ጋር ተያይዞ የነበረው ጉዳያቸው ስለመፈታቱ ተነግሮ የነበረው የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቹን በዚህ ጨዋታም እንደማይጠቀም ታውቋል።
ሲዳማ ቡና ባለፈው ሳምንት ስሑል ሽረን 4-1 በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሶ በጥሩ መነቃቃት ላይ ይገኛል። ቡድኑ በጠንካራ ተከላካይ ክፍል እና ውጤታማ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ የሚመማመን ቢሆንም ዐምና ያጣውን የቻምፒዮንነት ክብር ዘንድሮ ለማሳካት ከሜዳ ውጪ ያለውን ሪከርድ ማሻሻል ይጠበቅበታል። የነገው ጨዋታም የዚህ አካል ነው።
የቡድኑ ተቀዳሚ ምርጫ የመልሶ ማጥቃት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በነገው ጨዋታ ከግብ ክልሉ ለመራቅ እምብዛም የማይደፍረውና አብዛኛዎቹ ተጫዋቾቹን ከኳስ ጀርባ የሚያደርገው ጅማን የኋላ ክፍል በምን መልኩ አስከፍተው ውጤት ይዘው ይወጣሉ የሚለው ተጠባቂ ጉዳይ ነው።
ሲዳማ ቡና ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነ ስብስብ ይዞ የነገውን ጨዋታ ያደርጋል።
እርስ በርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን አራት ጊዜ ተገናኝተው ጅማ አባ ጅፋር ሁለቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ሁለቱን ጨዋታዎች ያለ ጎል በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። ጅማ 4፣ ሲዳማ 1 ጎል አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3/4-5-1)
ሰዒድ ሀብታሙ
ወንድማገኝ ማርቆስ – ከድር ኸይረዲን – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ
ንጋቱ ገ/ሥላሴ – ሄኖክ ገምቴሳ – ኤልያስ አህመድ
ኤርሚያስ ኃይሉ – ብሩክ ገብረዓብ – ተመስገን ደረሰ
ሲዳማ ቡና 4-2-3-1
መሳይ አያኖ
ዮናታን ፍሰሀ – ጊት ጋትኮች – ሰንደይ ሙቱኩ – ግሩም አሰፋ
ግርማ በቀለ – አበባየው ዮሐንስ
ሀብታሙ ገዛኸኝ – ዳዊት ተፈራ – አዲስ ግደይ
ይገዙ ቦጋለ
© ሶከር ኢትዮጵያ