ኢትዮጵያ መድን 2-2 ባህርዳር ከተማ ታክቲካዊ ትዝብቶች

የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች በሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ እሁድ እለትም ቃሊቲ ክራውን ሆቴል አከባቢ በሚገኘው የመድን ሜዳ ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡ ሁለቱ የአማራ ክልል ተወካዮች ወሎ ኮምቦልቻ ሰበታ ከተማን፤ ባህርዳር ከተማ ደግሞ ኢትዮጵያ መድንን ገጥመው ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡

በ9፡00 የተካሄደ የዕለቱ የመድን ሜዳ ሁለተኛ ጨዋታ ነው፡፡ የተመልካች ቁጥርም አነስተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ መጠነኛ ንትርኮች ግጭቶችም ተስተውለውበታል፡፡ በማጥቃት ወረዳ የሚደረጉ ቅብብሎችም ስኬታማነታቸው አናሳ ነበር፡፡
በማጥቃት ሒደት የተጋጣሚን ተከላካዮች የሚያልፉ ኳሶች ተከላካይ ሰንጣቂ ቅብብሎች (Through-Balls) ጥልቀት ያለው እይታ፣ ምጣኔ (ልኬት)፣ ኳሱን የሚቀበለው ተጫዋች ያላገናዘበ የአሰጣጥ ግምት ጎድሏቸው ተመልክተናል፡፡

በሁለቱም ቡድኖች እንደነዚህ ያሉ ቅብብሎች በትክክል ሲተገበሩ አልተመለከትንም፡፡ ለማጥቃት ወደፊት የሚላኩ ኳሶች የተቀባዩን ተጫዋች ፍጥነት፣ የቦታ አያያዝ እና ተከታዩን እንቅስቃሴ የመረዳት ችሎታ ግምት ውስጥ ማስገባትን ይጠይቃሉ፡፡
በጨዋታው ሌላ ትዝብት ውስጥ የሚጥሉ ሁነቶች ነበሩ፡፡ ቴክኒካዊ እና ታክቲካዊ ምክሮች በተመሳሳይ ሰዓት ከዋና አሰልጣኝ፣ ከምክትል አሰልጣኝ እና ከተቀያሪ ተጫዋቾች ሳይቀር ሲሰጥ ተስተውሏል፡፡ ተጫዋቾችን (በሜዳ ውስጥ የሚገኙ) ከማወናበድ የዘለለ ፋይዳ የሚኖረው ስለማይመስለን ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

IMG_1206

ባህርዳር ከተማ

ባህርዳሮች ብዙ ልምድ ያላቸው የተከላካይ ተጫዋቾች ባለቤት ናቸው፡፡ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድን እና ደደቢት የመሃል ተከላካይ መንግስቱ አሰፋ የቡድናቸው ወሳኝ የመሃል ተከላካይ ነው፡፡ መንግስቱ በጨዋታው በርካታ ኳሶችን ከግብ ክልል ሲያርቅ ውሏል፡፡
በመጠነኛ የHigh-line Defending System ሲጠቀም የነበረው የአማራው ክልል ቡድን ተከላካይ ክፍሉ ላይ ዝርግ የመሆን ችግር ይታይበት ነበር (Flat Back-4)፡፡ ይህም ቡድኑን በማጥቃት አጨዋወት ሒደት ማዕዘናትን ሲያጠቡበት ነበር፡፡ ውብሸት ካሳዬ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ላይ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ያላገናዘበ የቦታ አጠባበቁ ቡድኑ በመስመር ሊኖረው የሚገባውን የመቀባበያ አማራጭ ሲያሳጣ ነበር፡፡ ባህርዳር በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ አቻ የሆነበትን ግብ ተዘራ ጌታቸውከቀኝ መስመር በተመስገን ምህረቴ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ አስቆጥሯል፡፡

ኢትዮጵያ መድን

ከተጋጣሚያቸው የመከላከል አጨዋወት ስልት አንፃር የመድን አጥቂዎች በተደጋጋሚ ከባህርዳር ተከላካዮች ጀርባ ይገኙ ነበር፡፡ሆኖም አብዛኛውን ግዜ ከጨዋታው ውጪ ይሆናሉ፡፡ ከጨዋታ ውጪ ወጥመድ አጠባበቅን ያላማከለ ጉልበት እና ፍጥነት የተዋሃደበት ሩጫቸው ብዙም ስኬታማ አልነበረም፡፡
ቢኒያም ትዕዛዙ በቀኝ መስመር ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረ የመድን የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ነው፡፡ ቢኒያም overlap የሚያደርግበት የጨዋታ ሂደት እና እይታው ጥሩ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ መድኖች ተሻጋሪ ኳሶችን በጥሩ ሁኔታ ለመጠቀም ይሞክራሉ፡፡ ባህርዳር መሪ የሆነበትን ግብ ውብሸት ካሳዬ ካስቆጠረ በኃላ ሀብታሙ ወልዴ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር ለመድን አንድ ነጥብ ለማስገኘት ችሏል፡፡

IMG_1213

ያጋሩ