የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር በተሻጋሪ ቅጣቱ የመጨረሻ ጨዋታ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 2–1 ተሸንፏል።
አባ ጅፋሮች ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለ ጎል በአቻ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ ከተጠቀመባቸው ተጫዋቾች መካከል ጀሚል ያቆብን በአምረላ ደልታታ በመተካት ብቻ ወደ ሜዳ ሲገቡ፤ በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ስሁል ሽረን በሜዳቸው 4-1 ከረቱበት ስብስባቸው አበባየው ዮሐንስን ብቻ በማሳረፍ ዮሴፍ ዮሐንስን በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ፌደራል ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ ባጫወተው እና ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በዓምላክ ተሰማ አራተኛ ዳኛ በመሆን በተካሄደው በዚህ ጨዋታ ሊጉ ከተጀመረ በሦስተኛው ሳምንት ውስጥ ከታዩት እጅግ ማራኪ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ነበር ቢባል ማጋነን አይደለም። ጎል አስቆጥሮ ወደመከላከል ማፈግፈግ በሚተኮርበት ሊጋችን ጎል አስቆጥሮ ተጨማሪ ጎል ፍለጋ ማጥቃት ላይ ያማመዘን እና ጥሩ ፍሰት ያለው እግርኳስ መጫወት የዛሬው ጨዋታ ልዩ ነፀብራቅ ነበር።
በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ማጥቃቱ ሽግግር የሚገቡት ሲዳማዎች ገና በ2ኛው ደቂቃ መሐል ሜዳ ላይ እግሩ ስር ኳስ ሲገባ ለማን መስጠት እንዳለበት አስቀድሞ የሚያስበው ዳዊት ተፈራ በግሩም ሁኔታ ከተከላካዮች መሐል አሻግሮ ለአዲስ ግደይ አቀብሎት የጅማው ግብጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙን በግንባሩ በማለፍ ጎል አስቆጠረ ሲባል ኳሱ ረዝሞበት ወደ ውጭ የወጣው የጨዋታው የመጀመርያ የጎል እድል ነበረች።
ሲዳማዎች ወደ ፊት በመሄድ የጅማዎችን የግብ ክልል ረብሸው ሲመለሱ በአፀፋው ጅማዎች የሚፈጥሩት አደጋ ተሳክቶላቸው በአራተኛው ደቂቃ ማዕዘን ምት አግኝተው ኤርምያስ ኃይሉ በግንባሩ በመግጨት ጎል አስቆጥሮ ጅማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ይህች ጎል ለጅማ አባ ጅፋር የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጎል ሆኖ ተመዝግባለች።
የጨዋታው እንቅስቃሴ ክፍት ከመሆኑ አንፃር በቀጣይ ደቂቃዎች ጎል እንደሚቆጠር ያመላክት ነበር። ከወገብ በታች ያሉት የሲዳማ ቡና አጥቂዎች የሚፈጥሩት አደጋ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ የሆነባቸው ጅማዎች በ10ኛው ደቂቃ ጎል ሊቆጠርባቸው ግድ ሆኗል። ቀኝ መስመር ላይ ራሱን ነፃ አድርጎ ኳስ የሚጠባበቀው ሀብታሙ ገዛኸኝ ከዳዊት ተፈራ የተቀበለውን በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል ያሻገረውን በዚህ ውድደር ዓመት ክስተት ሆኖ ብቅ ያለው ይገዙ ቦጋለ በግሩም ሁኔታ ዘሎ በግንባሩ በመግጨት ኳሱን መረብ ውስጥ ከቶታል።
ይህ የወደፊት ተስፈኛ አጥቂ ጎል ካስቆጠረ በኃላ ኳሱን ከመረብ ውስጥ አውጥቶ ወደ ተመልካች በመሄድ ኳሱን የጠለዘበት መንገድ እና የተቀመጠ የውሃ ኮዳን በግሩ በመምታት ያሳየው ያልተገባ ባህሪ በቀጣይ ሊታረም የሚገባ ጉዳይ ነው።
ብዙም ሳይቆይ በ12ኛው ደቂቃ የሲዳማ ቡና ተከላካዮችን መዘናጋት እና ስህተት በመጠቀም ጅማዎች ያገኙትን ኳስ ሄኖክ ገምቴሳ ለኤርምያስ ኃይሉ አመቻችቶ ሰጥቶት ኤርሚያስ አንዴ ብቻ ወደ ፊት ኳሱን ገፋቶ ወደ ጎል የመታውን የሲዳማ ግብጠባቂ መሳይ እንደምንም ወደ ውጭ ያወጣበት ለቡድኑም ለራሱ ሁለተኛ ጎል መሆን የምትችል እድል ነበረች።
አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ያልዘገዩት ሲዳማዎች በ15ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ በሁለት ተከላካዮች መሐል በጥሩ ሁኔታ አሾልኮ ነፃ ኳስ ከግብ ጠባቂው ሰዒድ ጋር አገናኝቶ የሰጠውን ሀብታሙ ገዛኸኝ ወደ ጎል ቢመታውም ግብጠባቂው ሰዒድ በጥሩ ሁኔታ ያዳነበት ጎል መሆን የሚችል ሌላ ተጨማሪ እድል ነበር።
በተወሰነ መልኩ ወደ ኃላ አፈግፍገው መጫወት የጀመሩትን የጅማዎች መከላከልን ለማስከፈት ኳሱን ወደ ኋላ በመመለስ በሁሉም የሜዳ ክፍል አደራጅተው ቀዳዳ ፍለጋ የሚያድርጉት ቅብብል እና መናበብ፣ በዚህ ሂደት ውስጥ ሲዳማዎች ኳስ ሲነጠቁ በምላሹ የሚነጠቁትን ኳስ መልሰው ለመቀበል በማፈን የሚያደርጉት ጥረት ልዩ ነበር።
እጅግ አዝናኝ እና ሳቢ ሆኖ የቀጠለው ይህ ጨዋታ ምንም እንኳ ተጨማሪ ጎል ለመመልከት ለጊዜው ባንችልም እንቅስቃሴያቸው ጥሩ ነበር። በተለይ በሁለት አጋጣሚ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የተሰራ ጥፋት እየተመለከቱ የዕለቱ ዳኛ በዝምታ ማለፋቸው ጅማ አባ ጅፋሮችን የቡድን አባላት ተቋማቸውን እንዲያሰሙ አድርጓቸዋል። በማጥቃት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ በመከላከሉ ሽግግር ላይ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች በሚፈጥሩት ክፍተት ተከትሎ 43ኛው ደቂቃ አምረላ ደልታታ ጥሩ ኳስ አግኝቶ ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ ጅማዎችን መሪ በማድረግ ወደ እረፍት እንዲያመሩ የሚያደርግ እድል ነበረች።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው ፈጣን እንቅስቃሴ ቀጥሎ በ47ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከመስመር ወደ ጎል አጥብቦ በመግባት ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው አዲስ ግደይ አቀብሎት አዲስ በሚታወቅበት መንገድ ጎል አስቆጥሮ ሲዳማን 2-1 እንዲመሩ አስችሏል። ሁሌም አዲስ ግደይ በሚያስቆጥራቸው ጎሎች ጀርባ ትልቁን ሚና የሚወጣው ሀብታሙ ገዛኸኝ ለዚህችም ጎል መቆጠር ጉልህ አስተዋፆኦ ነበረው።
ከፊት ያሉት የሲዳማ ቡና ሦስት አጥቂዎች እረፍት አልባ እንቅስቃሴ ቀጥሎ በ55ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችል እድል ሀብታሙ ገዛኸኝ ከመስመር ወደ ሳጥን ውጥ በመግባት ተከላካይ አሸማቆ በማለፍ ወደ ጎል ቢመታውም ጎል መሆን የሚችሉ ዕድሎችን ሲያመክን የቆየው ግብጠባቂው ሰዒድ አድኖበታል።
አልፎ አልፎም ቢሆን ወደ ጎል የሚደርሱት ጅማዎች በ58ኛው ከደቂቃ ከማዕዘን ምት ሲሻማ ተደርቦ የተመለሰውን ኳስ በጎሉ የቅርብ ርቀት አምረላ ደልታታ አግኝቶ ወደ ጎል ቢመታው ግብጠባቂው መሳይ እንደምንም ተንሸራቶ ወደ ውጭ ያጣበት ለጅማዎች አቻ መሆን የሚችሉበት ዕድል ነበር።
በምን ደቂቃ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አስቸግሮ ባለፈው በዚህ ጨዋታ 60ኛው ደቂቃ በፈጣን እንቅስቃሴ ይገዙ ለአዲስ ግደይ አቀብሎት በፍጥነት ወደ ፊት በመሄድ ለሀብታሙ ገዛኸኝ ደገፍ አድርጎ የመታው ለጥቂት በግቡ ቋሚ ስር ወደ ውጭ ወቶበታል። ሌላ ሲዳማዎች የሚያስቆጭ ሌላ የጎል አጋጣሚ 68ኛው ደቂቃ ይገዙ ቦጋላ ለአዲስ ግደይ ሰቶት ከመስመር ወደ ጎል አጥብቦ በመምታት ከግብጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ኳሱን ሰዒድን አልፎ ጎል ሆነ ሲባል መላኩ ወልዴ ኳሱ ላይ ደርሶ ወደ ውጭ አውጥቶበታል።
ከ70ኛው ደቂቃ በኃላ ጅማዎች የአቻነት ጎል ፍለጋጫና ፈጥረው እየተጫወቱ ባለበት ወቅት የማጥቃት ኃይላቸው የሆነው ኤርምያስ ኃይሉ ጉዳት አጋጥሞት ተቀይሮ መውጣቱ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴን አሳንሶታል። ያም ቢሆን አምረላ በተለይ በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ጎል ያስቆጠረ ቢሆንም የዕለቱ ዳኛ ጎሉን የሻሩበት መንገድ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባለማወቅ በዳኛው ላይ ተቃውሟቸውን አሳይተዋል። ጨዋታውም ጥሩ ፉክክር አስመልክቶን በመጨረሻም በሲዳማ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎችተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ማሸነፍ ሲችሉ በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋሮች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት አስተናግደዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ