የአሰልጣኞች አስተያየት | መቐለ 70 እንደርታ 1-1 ኢትዮጵያ ቡና

በሳምንቱ ተጠባቂ የነበረው የመቐለ እና ኢትዮጵያ ቡና በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱም. ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።

“በተጫዋቾቻችን ላይ የሥነ-ልቦና ጫና እየታየ ነው” ገብረመድህን ኃይሌ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ሁለት መልክ ነበረው። የመጀመርያው አጋማሽ ቡድናችን ትኩረቱን ያጣበት ጊዜ ሲሆን ሁለተኛው አጋማሽ ግን በሙሉ አቅማችን ለማጥቃት የሞከርንበት ነበር። ያገኘናቸው ዕድሎች መጠቀም አልቻልንም።

በተጫዋቾቻችን ላይ የሥነ-ልቦና ጫና እየታየ ነው። የውድድሩ አሸናፊ ስለሆንን ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ይጠበቅብናል። እሱ ሳይሆን ሲቀር ደሞ ጫናዎች እንዳሉ የታወቀ ነው። እንደ ቡድን የመጫወት አቅማችን ጥሩ አይደለም። የተናጠል ጨዋታ እየበዛ ነው፤ በቀጣይ ይህንን አስተካክለን እንመጣለን።

“በሚቀጥለውም ይህን መንፈስ ይዘን ነው ለማሸነፍ የምንጫወተው” ካሣዬ አራጌ

ጨዋታው ጥሩ ነበር። መቐለዎች በሚጣሉ ኳሶች ጫና በመፍጠር በዛ መንገድ ነው የጎል ዕድል የፈለጉት። እኛም የሚመጡትን ኳሶች ተቆጣጥረን የመጫወት ሂደት ነበር። እንደዚ አይነት ነበረው አብዛኛው የጨዋታው መልክ። እኛ ሁሌ ለማሸነፍ ነው የምንጫወተው፤ ከዛ በኋላ ግን ሜዳ ውስጥ ያለውን ነገር ይወስነዋል። የቡድኑ መንስፈስ በሜዳችም ይሁን ከሜዳችም ውጭ ለማሸነፍ ነው። በሚቀጥመውም ይህን መንፈስ ይዘን ነው ለማሸነፍ ምንጫወተው።

ስለ አጨዋወቱ እና ስለሚፈጠሩት ስህተቶች

ዛሬ ብዙ ስህተቶች አልተፈጠሩም። ያልተፈጠሩት ለምንድነው ተጫዋቾቻችን ሃላፊነት ወስዶ ለመጫወት አልደፈሩም። ግብ ጠባቂያችንም ኳሶች በረጅሙ ይልክ ነበር፤ መጫወት ነበረብን። ስህተቶችን እያረምን ነው የምንሄደው። ግን ያንን በትክክል እያደረጉት አልነበረም። ሃላፊነት ለመውሰድ እየፈሩ ነበር ያንን ችግር ይታይ ነበር። እንደዛ ስንጫወት የሚፈጠሩ ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን እንቅስቃሴው ይዘን መቀጠል ነበረብን፤ ዛሬ ግን ያ በብዛት አልነበረም።


© ሶከር ኢትዮጵያ