ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዳማ ከተማ ከሜዳው ውጪ ሲያሸንፍ ሀዋሳ እና ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው አዳማ ከተማ ከሜዳው ውጪ አርባምንጭን 1ለ0 ሲረታ ሀዋሳ በሜዳው ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ ጋር 1ለ1 ተለያይቷል፡፡

አርባምንጭ ላይ 9:00 ሲል ባለሜዳው አርባምንጭ ከተማ የአምናው ቻምፒዮን አዳማ ከተማ ገጥሞ ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡ አዳማ ከተማ የተሻለ በነበረበት እና ወደ አዳማ የግብ ክልል ለመድረስ የተቸገሩት አርባምንጮች ገና በጊዜ በተቆጠረባቸው ግብ ተሸንፈዋል፡፡ በ5ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ ብቸኛ የአዳማን ግብ ከመረብ አሳርፋ ጨዋታው ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ግብ ሳይቆጠርባቸው 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት ተደምድሟል፡፡

ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ሀዋሳ ከተማ በሊጉ ሁለተኛ ጨዋታውን ባደረገበት እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንፃሩ የመጀመሪያውን የሊግ መርሀ ግብር በተስተካካይነት ተይዞለት የመጀመሪያ ጨዋታውን በአዲሷ አሰልጣኝ መሠረት ማኔ እየተመራ ከሜዳው ውጪ አድርጎ አንድ ነጥብ ይዞ ወጥቷል፡፡ 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ አሰልቺ የኳስ ቅብብሎች በእለቱ ከነበረው ከባድ ፀሀይ ጋር ተደምሮ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የጠራ የግብ ዕድልን ለመመልከት ግማሽ ሰዓት ያህል ፈጅቷል፡፡

31ኛው ደቂቃ ላይ የቀኝ መስመር ተጫዋቿ ወርቅነሽ ሜልሜላ በግራ እግራ በግራ የሀዋሳ የግብ ክልል ያሻማችውን ኳስ የሀዋሳ ተከላካዮችን መዘናጋት ተጠቅማ ነፃ ቦታ ላይ ቆማ የነበረችው መሳይ ተመስገን አግኝታው ከመረብ አሳርፋ ኤሌክትሪክን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡

ሀዋሳዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የማጥቃት አካሄዳቸውን በይበልጥ ወደ ቀኝ በኩል አዝንብላ ስትጫወት ወደነበረችሁ መሳይ ተመስገን ሀዋሳዎች ማዞር ቢችሉም ተጫዋቿ ወደ መጨረሻ የግብ ክልል ስትደርስ በቀላሉ በኤሌክትሪክ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች ሲወጣ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ኤሌክትሪኮች ሁለተኛ ግብ ሊሆን የሚችል መልካም አጋጣሚን በድጋሚ አግኝተው መጠቀም አልቻሉም፡፡ ሰሚራ ከማል መሬት ለመሬት የተሰጣትን ኳስ በቀጥታ መታ የግቡ ቋሚ ብረትን ነክቶ የተመለሰባትም ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች፡፡ ቢያንስ አቻ ሆነው ወደ መልበሻ ለማምራት በተወሰነ መልኩ ሲጥሩ የነበሩት ሀዋሳዎች ዓይናለም አደራ ከመስመር አሻምታ የኤሌክትሪኳ አምበል እታፈራሁ አድርሴ በራሷ ላይ ለማስቆጠር ተቃርባ በፍጥነት ግብ ጠባቂዋ ትዕግስት አበራ አወጣችባት እንጂ አቻ ሆነው ለእረፍት ሊያመሩ ተቃርበው ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ ፍፁም መሻሻሎች አድርጎ ሲገባ ኤሌክትሪክ ደግሞ መሪነታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት በሚመስል መልኩ ግብ ክልላቸውን አጥረው ውለዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሻሽለው ለመቅረባቸው አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የወሰደው የተጫዋች ቅያሪ ትልቁን ቦታ ይይዛል። አሰልጣኙ በቅያሪያቸው ዓይናለም አሳምነው እና ቅድስት ቴቃን በማስወጣት ሳራ ኬዲ እና ይታገሱ ተገኝ ወርቅን ማስገባታቸው የጠቀማቸው መሆኑን አይተናል፡፡ በተለይ አማካዩዋ ሳራ የጨዋታውን የመሀል ሜዳ ሚዛን በመጠበቅ ወደ አጥቂዎቹ ስትልክ የነበረበት ሂደት ጎልቶ ቢታይም የአጨራረስ ክፍተት ግን በቀላሉ ግብ እንዳያስቆጥሩ አዳጋች ሆኖባቸው ውሏል፡፡ አጥቂዎቹ ነፃነት መና እና ይታገሱ ተገኝወርቅ ቶሎ ቶሎ ኳሶችን አግኝተው የማስቆጠር እድሎችን ቢያገኙም የቀድሞ ክለቧን በተቃራኒው የገጠመችው የኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ ትዕግስት አበራ በድንቅ ብቃት ታግዛ ደጋግማ አድናባቸዋለች፡፡

55ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች ተሳክቶላቸው ተደጋጋሚ ኳሶችን በቀላሉ ስታባክን የነበረችው መሳይ ተመስገን በግራ በኩል ወደ ሳጥን ገብታ ያቀበለቻትን ካሰች ፍሰሀ ከመረብ አሳርፋ ሀዋሳን አቻ አድርጋለች፡፡ 60ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ተከላካይ ቅድስት ዘለቀ በኤሌክትሪክ የመስመር ተጫዋች ወርቅነሽ ሜልሜላ ላይ አደገኛ ጥፋት ፈፅማ የእለቱ ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በዝምታ ማለፏ አግራሞት የጫራ ሲሆን ጉዳት በጉልበቷ ላይ የገጠማት ወርቅነሽም እየተንሰቀሰቀች በማልቀስ ከሜዳ ተቀይራ ወጥታለች፡፡

የማሸነፊያ ግብ ለማግኘት ያለመታከት ሲያጠቁ የነበሩት ሀዋሳዎች በመሳይ ተመስገን ይታገሱ ተገኝወርቅ እነና ነፃነት መና የማግባት ዕድሎችን ቢያገኙም አስደናቂ በነበረችው ትዕግስት አበራ ሲከሽፉ ተስተውሏል፡፡ በተለይ በጭማሪው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ይታገሱ ፊት ለፊት ያገኘችውን ኳስ አስቆጠረች ተብሎ ሲጠበቅ ትዕግስት መልሳባታለች፡፡

ሙሉ ዘጠናው ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ሰአት የኤሌክትሪኳ የግራ መስመር ተጫዋች እና ለቡድኗ ግብ ያስቆጠረችሁ መሳይ ተመስገን ለሀዋሳ ቅጣት ምት በተሰጠበት ወቅት የእለቱ ዳኛ የፊሽካውን ድምፅ ሳታሰማ ቀድማ ኳሱን ለመምታት በመሞከሯ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ወጥታለች፡፡ ጨዋታውም 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

* ማስታወሻ – በሁለቱም ቡድኖች በኩል መሳይ ተመስገን የተባሉ ተጫዋቾች መኖራቸው ልብ ይሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ