ጥያቄ እየተነሳበት ያለው የሶዶ ስታዲየም መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ ላይ ነው

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተደረጉ ሁለት የሶዶ ስታዲየም ጨዋታዎች አሰልጣኞች በተደጋጋሚ ቅሬታ እያሰሙበት የነበረው የወላይታ ድቻ ሜዳ አፋጣኝ ማሻሻያ እየተደረገበት ነው፡፡

በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ሲዳማ ቡናን በሜዳው በረታበት ጨዋታ ላይ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሲዳማ ቡና እና የባለሜዳው ክለብ ወላይታ ድቻ አሰልጣኞች ሜዳው ምቹ አለመሆኑን በነበራቸው ድህረ አስተያየት መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዐቢይ ኮሚቴ ከአሰልጣኞቹ አስተያየት በመነሳት ለክለቡ በአፋጣኝ ሜዳው እንዲስተካከል ትዕዛዝ በማስተላለፍ የተነሳ የተወሰነ ማስተካከያን በመጫወቻ ሜዳው ላይ ማድረግ ጀምሯል፡፡ በሁለተኛው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከመጫወቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የማስተካከል ሥራውን የጀመረ ሲሆን ከሰሞኑንም አፋጣኝ የሰው ኃይልን በመጠቀም አመቺ ባልሆኑት የሜዳው አካላት ላይ ተገቢውን ዕድሳት በመስራት ለቀጣዩ ጨዋታ ለማድረስ መዘጋጀታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው በመገኘት ከክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሆሲሶ ጋር ባደረገችው ቆይታ ለመገንዘብ ሞክራለች፡፡

ገና ሊጉ ረጅም ጉዞን መጓዝ ባልቻለበት በአሁኑ ጊዜ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲነሱበት የነበረው የሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ በቀጣዩ ለሚያደርገው የሊግ መርሀ ግብር በምን ዓይነት መልኩ ሜዳው ከነበሩበት ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ይፀዳ ይሆን የሚሉ ሀሳቦች የሚጠበቁ ጉዳዮች ሲሆኑ በተመሳሳይ የሀዲያ ሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ሜዳ የማሻሻያ ሥራዎች እንዲፈፀሙ የፕሪምየር ሊጉ ዐቢይ ኮሚቴ ትዕዛዝ ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ መሆኑንም ሰምተናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ